Fana: At a Speed of Life!

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ማስተላለፍ እንደማይቻል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ የእጅ ምልክትን ጨምሮ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ማስተላለፍ እንደማይቻል ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቀጣዩ ሃምሌ ወር በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለተወዳዳሪ አትሌቶች በተከለከሉ የደስታ አገላለጾች እና የሚያስተላልፏቸውን መልዕክቶች በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህም አትሌቶች በመወዳደሪያ መድረኮች እና በሽልማት ስነ ስርአት ወቅት፥ በእጅ ምልክት፣ በመንበርከክ እና በመሰል እንቅስቃሴዎች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ማስተላለፍ አይችሉም ብሏል።

ማንኛውም አይነት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መልዕክትም በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ተቀባይነት የለውም ነው ያለው።

ይህን ተላልፈው የሚገኙ ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በስፖርት የበላይ አስተዳዳሪ አካል እና በብሄራዊ ኢሊምፒክ ኮሚቴ የስነ ምግባር እርምጃዎች ይወሰድባቸዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን በማህበራዊ ትስስር ገጾች፣ በሚዲያ እና በቡድን ስብሰባ ወቅት ያላቸውን ፖለቲካዊ አመለካከትም ሆነ መልዕክት መግለጽ ይችላሉ ተብሏል።

ውድድሩ ስፖርት ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት እና ከማንኛውም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ነጻ ነው የሚለውን የኦሊምፒክ ኮሚቴውን መርህ የጠበቀና ያከበረ መሆን አለበትም ነው የተባለው።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.