Fana: At a Speed of Life!

በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል – በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በአዲሱ አመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ የፈረንጆቹን አዲስ አመት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ 2020 ቻይና እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 50ኛ አመት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

አያይዘውም አመቱ የእስካሁን ስኬቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት አመት ይሆናልም ነው ያሉት።

የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በ2020 ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፥ በኢኮኖሚውና በግብርናው መስክም የሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ስራዎች መሰራታቸውንም ነው የተናገሩት።

በርካታ የቻይና ኩባንያዎችና የቻይና ባለሃብቶች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ለያዘው እቅድ አጋዥ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ቻይና በአፍሪካ የምትገነባውን የበሽታ መከላከያ ማዕከል መቀመጫ በአዲስ አበባ የማድረግ እቅድ እንዳላትም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍም በተሻለ ትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው፥ ቻይና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎችን ትደግፋለችም ነው ያሉት በንግግራቸው።

መጭው ሀገራዊ ምርጫም ሰላማዊ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል አምባሳደር ታን ጂያን።

በሃብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.