Fana: At a Speed of Life!

በነዳጅ ማደያዎች የሚታዩ ሰልፎችን ለማስቀረት እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አባባ ፣ ሚያዚያ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የነዳጅ ማደያዎች የሚስተዋሉ ሰልፎችን ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተለይም በአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎች እየተፈጠሩ ያሉ ሰልፎችን በተመለከተ ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም ከነዳጅ ኩባንያ ማህበራት ጋር ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የሴክተሩን አደረጃጀት፣ መሠረተ ልማት፣ የአሰራር ስርዓት በመፈተሽ መስተካከል ያለባቸውን መመሪያዎችና ደንቦች መነሻ በማድረግ እየተሰሩ ያሉ ጥናቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጥናቶችን መሠረት በማድረግ ከነዳጅ ግዢ ስርዓት እስከ መጨረሻው ተጠቃሚዎች ድረስ በአቅርቦትና ጥራት ዙሪያ በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

መንግስት የነዳጅ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ችግርን ለመፍታት በቂ ተሽከርካሪ ለማስገባት እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በስራ ላይ ያሉትን ተሽከርካሪዎች በአግባቡ መጠቀምና ክትትል ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

ሆኖም አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎችና ተጠቃሚዎች እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርግ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን በማውሳት፥ በቀጣይ የቁጥጥር ስርዓቱን በማሳደግ ወደ ተግባር ስለሚገባ የነዳጅ ማደያዎች ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኢትዮጵያና ጂቡቲ የሚገኙ ዴፖዎች በቂ ክምችት ያላቸው በመሆኑ በአቅርቦት ላይ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ ነው የገለጸው።

የአቅርቦት ችግር ባለመኖሩ ሁሉም ህብረተሰብ ውድ ጊዜውን ሰውቶ አላስፈላጊ ሰልፍ ከመፍጠር ተቆጥቦ ተረጋግቶ ስራውን እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን ከንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.