Fana: At a Speed of Life!

በንግድና አገልግሎት የተሰማሩ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 120 ሚሊየን ብር አተረፉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ስር የሚገኙ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ አምስት የልማት ድርጅቶች በ2013 በጀት የመጀመሪያው አጋማሽ ዓመት 119 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር አተረፉ፡፡

ይህ ተገለጸው የድርጅቶቹ የዕቅድ አፈጻጸም የኤጀንሲውና የልማት ድርጅቶቹ ቦርድ እና አስተዳደር አባላት ባካሄዱት ስብሰባ ነው ተብሏል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ ይህንን ትርፍ ያገኙት በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የንግድ፣የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት በመስጠት 2 ነጥብ 76 ቢሊየን ብር ሽያጭ ገቢ በማግኘታቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣ ፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት፣ ግዮን ሆቴል ድርጅት እና የልማትና ሆቴል ማህበር አክሲዮን ማህበር (ሂልተን ሆቴል) ናቸው፡፡

ከእነዚህ የልማት ድርጅቶች አራቱ የውጭ ሽያጭ የሚያከናውኑ በመሆኑ በአጋማሽ ዓመቱ 9 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በማግኘት የዕቅዳቸውን 55 ነጥብ 6 በመቶ ማከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡

በኦፕሬሽን አፈጻጸም በተለይም በሽያጭ ገቢ ብር 2 ነጥብ 3 ቢሊየን በማግኘት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በመቀጠልም የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት 252 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡

በንግድ፣ ቱሪዝምና ሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ኮቪድ-19 ባስከተለው ተጽዕኖ የተነሳ ብዙዎቹ ለኪሳራ በተዳረጉበት ወቅት በኤጀንሲው ሥር ያሉት ድርጅቶች አፈጻጸም የተሻለ ሆኖ መገኘቱ አበረታች መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

በቀጣዩ መንፈቅ ዓመት ጠንክረው በመሥራት የዓመቱን ግብ እንዲያሳኩ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ማሳሰባቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.