Fana: At a Speed of Life!

በንጹሃን ላይ የተፈጸመን ጥቃት መነሻ በማድረግ ክልሉን ለማተራመስ የሚሰሩ ሃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል – የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወለጋ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት መነሻ በማድረግ የአማራ ክልልን በሰልፍና በግርግር ለማተራመስ በማቀድ እየሰሩ ያሉ ሃይሎች ለጠላት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለሙ በመሆናቸው ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አሳሰቡ።

ዋና ዳይሬክተሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ በወለጋ በንጹሃን ላይ ጥቃት በፈጸሙ አካላት ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጅ ይህን ገልብጠው በሰልፍና በግርግር ክልሉን ለማተራመስ በማቀድ እየሰሩ ያሉ ሃይሎች ለጠላት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለሙ በመሆናቸው ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የውስጥ አንድነት ሊያጠናክር የሚችል ህጋዊ ስርአት በመዘርጋት የህግ ማስከበር ስራ በሁሉም አከባቢ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት በክልሉ እየተካሔደ የሚገኘውን የህግ ማስከበር ሒደት መገምገሙንም አንስተዋል።

መነሻውን የህዝብ ጥያቄ ያደረገው የክልሉ የህግ ማስከበር ስራ መልካም ውጤትና እና ትምህርት የተገኙበት እንዲሁም ሰላም ጠያቂውን ማህበረሰብ ከነበረው ስጋት አላቆ እፎይታን ያስገኘ እንደነበረም በጸጥታው ምክር ቤት ተመላክቷል ብለዋል።

ክልሉ ከነበረው የስርዓት አልበኝነት ነባራዊ ሁኔታ ተላቆ ወደተጨባጭ የልማት እንቅስቃሴ ሊያሸጋግር የሚችል ምዕራፍ ላይ ደርሷል ያሉት ሃላፊው፥ በዚህ የህግ ማስከበር ዘመቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍርደኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ፍርደኞቹ መካከል የጸጥታ ሃይሉን የከዱ እና የመንግስትን መሳሪያ የሸጡ እንደሚገኙበት በመጥቀስም፥ እነዚህ ፍርደኞች ተይዘው በህግ እንዲዳኙ የተደረገው ለጸጥታ መዋቅሩ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ መሆኑን ገልፀዋል።

ለጠላት እየተላላኩ ያሉ የሽብር ሃይሎች በአማራ ክልል እንዳይሳካላቸው በማድረግ እኩይ ዓላማቸውን ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል።

የውጭና የውስጥ ሃይሎች የአማራ ክልል ለውጭ ጠላት ምቹና ደካማ ክልል እንዲሆን አልመው እየሰሩ እንደነበር ገልጸው ከላይ እስከታች የተዋቀረው ጠንካራ የጸጥታ ሃይል ይህ እንዳይሆን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

አያይዘውም በህግ ማስከበር ዘመቻው በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቅ መቻሉን ያነሱ ሲሆን ከህገ- ወጦች የተለቀቁ ቦታዎችንም ለህጋዊ አካላት የማስተላለፍ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

ጠላት ክልሎች እርስበርስ እንዳይግባቡና ህዝቡ እንዳይደማመጥ አድርጎ አሁንም እየሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም በወለጋ የተካሔደውን የዜጎች ኢ ሰብአዊ ጭፍጨፋ ለአብነት አንስተዋል።

ራስን ከውጭ ጠላት መከላከል የሚቻለውም ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት፣ ከስሜት በመውጣት እና በመደማመጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.