Fana: At a Speed of Life!

በንጹሃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈጸምን ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን- የብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት በማድረግ እየተካሄደ ያለውን ጥቃት አጥብቆ እንደሚያወግዝ የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ዜጎችን በማንነት ለይቶ በማጥቃት ምንም አይነት የፖለቲካ ትርፍ ሊገኝ አይችልም ብሏል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት የትኛውንም የህዝብ ክፍል የማይወክልና ኃላፊነት የማይሰማቸው የግጭት ነጋዴዎች ሴራ መሆኑን መላው የሀገራችን ህዝቦች ሊገነዘቡ ይገባልም ነው ያለው፡፡
በጨካኝ አረመኔ የጥፋት ኃይሎች ጥቃት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰው ላለው ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸን ለዘመናት ተከባብሮ ክፉና ደጉን አብሮ ያሳለፈን ህዝብ በማጋጨት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጣጣሩ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች የማይሳካላቸው መሆኑን አጥብቀን ልንገልጽላቸው እንወዳለን ሲል ገልጿል፡፡
በዜጎች ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውንና ችግሩ እንዲፈታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባልተወጡ የስራ ኃላፊዎች ላይ ጥብቅ ፖለቲካዊ፣ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን እንገልጻለን ብሏል፡፡
ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን ለፍቶ አዳሪ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው ብቻ ለይቶ በማጥቃት ሀገርንና ህዝብን ወደ ትርምስ ለማስገባት ተቀናጅተው የሚንቀሳቀሱ የውስጥም ሆነ የውጭ ጨካኝ የጥፋት ኃይሎችን አጥብቆ የሚያወግዝና በእነዚህ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ተወስዶ የዜጎች ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ብልጽግና ፓርቲ አጥብቆ የሚታገል መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ሲል ገልጿል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.