Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሕግ የማስከበር እርምጃ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ከ300 በላይ እና በደሴ ከተማ ከ100 የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ደግሞ በ1ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ለሕግ ቀርበዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ህግን ለማስከበር በተወሰደ እርምጃ ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ እንደገለፁት፥ ከማህበረሰቡና ማህበራዊ አደረጃጀቶች በተደጋጋሚ የሚነሳውን ‘‘የህግ የበላይነት ይከበር’’ ጥያቄ ለመፍታት በክልል እየተወሰደ ካለው እርምጃ ጋር ተያይዞ ዞኑም እርምጃ ወስዷል።

ከግንቦት 1 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ/ም ድረስ በተወሰደ እርምጃ 302 ሰዎች ተጠርጣሪ ሆነው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ እንደሆነም ነው የገለጹት።

የህዝብን ሰላም ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱ የተገለጸ ሲሆን፥ ማህበረሰቡ ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት በኩል ለነበረው ሚና አመስግነዋል።

የፋኖ አደረጃጀቶች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው የሚሠሩ ናቸው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አቶ ታደሰ ፥ ትናንትም ዛሬም ነገም የህዝብ ባለውለታዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን በፋኖ ስም የሚነግዱ አካላትን ተጠያቂ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን ፥ በአሁኑ ወቅት የጦር መሳሪያ የማስመዝገብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል፡፡

‘‘ምዝገባው ፋኖን ለማዳከም ነው’’ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ሐሰት መሆኑን ጠቁመው፥ በቀጣይ በዞኑ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተመሳሳይ የደሴ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውንና የከተማውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገልጸዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት ፥ በሂደቱም ከ100 ያላነሱ የሕዝቡን ሰላም ሲያናጉ፣ የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት ሲሞክሩ የነበሩ፣ ዘረፋ ሲፈጽሙ የቆዩና በሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ላይ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡

የሕግ ማስከበር ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የሕዝቡ ሚና ከፍተኛ ነበር ያሉ ሲሆን፥ በቀጣይ የሕግ ማስከበር ሥራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የሕግ የበላይነት እንዲከበር ከህብረተሰቡ በተነሳው ብርቱ ጥያቄና በመንግስት ቁርጠኝነት በተወሰደ ሕግ የማስከበር እርምጃ እስካሁን ድረስ በብሔረሰብ አስተዳደሩ 1ሺህ 113 የወንጀል ተጠርጣሪዎች ለሕግ ማቅረብ መቻሉን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛውገልጸዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የወንጀል ተጠርጣሪዎች መካከል 130 የሚሆኑት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ሲፈለጉ የነበሩ ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ በመግደል ሙከራ፣ በተደራጀ ዝርፊያ፣ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በአስገድዶ መድፈርና በልዩልዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

ህግ የማስከበር እርምጃው የታሰበውን ግብ ሙሉ በሙሉ አሳክቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው÷ ህብረተሰቡ በሕግ የሚፈለጉ የቤተሰብ አባላትን ሳይቀር አሳልፎ በመስጠት ለሕግ የበላይነት መከበር ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.