Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ሶስት የመካናይዜሽን ማእከላት ተቋቋመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ሶስት የመካናይዜሽን ማእከላት መቋቋማቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ፡፡

ማዕከላቱ የአርሶ አደሮች ምርት ለመሰብሰብ የሚጠቀሙት እና የሚያባክኑትን ከፍተኛ ጉልበት እንዲሁም ምርትን ከብክነት ለመታደግ ታልሞ መቋቋማቸውን ቢሮው ገልጿል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በክልሉ ያለው የመካናይዜሽን ሽፋን አነስተኛ መሆኑ ጠቅሰው፤ ሽፋኑን ለማሳደግ እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቢሮው የተያዘው በጀት ዓመት እስኪጠናቀቅ በዘር ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 500 ሺህ ሄክታር መሬት በትራክተር  እንዲታረስ እንዲሁም 816 ሺህ 601 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ደግሞ በዘመናዊ የመውቂያ መሳሪያዎች እንዲወቃ እቅድ መያዙንም ገልፀዋል።

አፈፃፀሙ ሲታይም ከያዘው እቅድ አንፃር የመካናይዜሽን ሽፋኑ ከ10 በመቶ መዝለል እንዳልቻለም ነው ያስታወቁት።

አሁን ላይ ግን የግብርና መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መወሰን የመካናይዜሸን ሽፋኑን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ ነው ተገልጿል።

የግብርና መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መወሰኑን ተከትሎም ለቀጣይ በተመረጡ ቦታዎች ባለሀብቶች እና ዩኒየኖች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እስከ ማዘጋጃ ድረስ በቅርበት እንዲሰሩ ይደረጋል ተብሏል።

በዚህም ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ጎጃም እና ምእራብ ጎንደር የተመረጡት ዩኒየኖችም በቀጣይ የምርት ጊዜ ለአርሶ አደሩ መሳሪያዎቹን ማቅረብ ይጀምራሉ ብለዋል ዶክተር መለስ።

አሁን በክልሉ ምእራብ እና ምስራቅ ጎጃም፣ ጎንደር እና መተማ ሶስት የመካነይዜሽን ማእከላት የተቋቋሙ ሲሆን፥ ማእከላቱ ምርት በስፋት የሚገኝባቸውና ለመካናይዜሽን ምቹ የሆኑ እንዲሁም አርሶ አደሩ በኩታገጠም የሚያለማባቸው ናቸው ተብሏል።

ማእከላቱም ለቀጣይ የምርት ጊዜ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ስራ እንደሚጀምሩም ነው የተገለፀው።

በማእከላቱ ለመግባት እና ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ለማቅረብ በርካታ ባለህብቶች ፍገጎት እያሳዩ ሲሆን፥ ተሳትፎን  ለማሳደግ እስከ ዞን ድረስ መሳሪያዎቹ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ብድር ለማመቻቸት ከልማት ባንክ ጋር እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ሀላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ተናግረዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.