Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በህወሓት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በአሸባሪው በህወሓት የወደሙ ከ4 ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ያወደማቸው የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አሸባሪው ህወሓት የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ በሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል ብለዋል።

ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የወደሙና የፈረራሱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር በሚደረገው ርብርብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

“የፈረሱት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት እንዳይሆኑ የጥራት ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ገንብቶ ለአልግሎት ማብቃት የግድ ነው” ብለዋል።

“ተቋማቱ በጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት ካልበቁ የአሸባሪውን ዕቅድ ማሳካት ስለሆነ የመልሶ ግንባታና ማደረጃቱ ሥራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል” ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማተቤ ታፈረ በበኩላቸው እንዳሉት፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆዩ የክልሉ አካባቢዎች ከ4ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን አውድሟል።
ትምህርት ቤቶች ገንብቶና ጠግኖ መልሶ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሃላፊው እንዳሉት ትምህርት ቤቶቹ በመውደማቸው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲሁም 116 ሺህ መምህራን ከሥራ ውጭ ሆነዋል።

የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባትና ቁሳቁስ አሟልቶ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ዶክተር ማተቤ ጥሪ አቅርበዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.