Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ የግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በመስኖ ልማቱ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የግብርና ምርምር ማዕከላት እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቋል።
የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በሰብል ላይ ያደረሰውን ውድመት ማካካስ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ መተካትን አላማ ያደረገ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 80 ሺ ሄክታር መሬት በማልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።
በልማት ስራው ላይ ሰባት ዩኒቨርስቲዎችና በክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኙ ምርምር ማዕከላት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ደባርቅ በበጋ ስንዴ ልማት እየሰሩ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው።
የባህር ዳር፣ የጎንደርና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች እያንዳንዳቸው ከ500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ በዘመናዊ መንገድ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን እያካሄዱ መሆናቸውንም ነው ዶክተር ሃይለማርያም የገለጹት።
በተጨማሪም በአማራ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኙ የምርምር ማዕከላት በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በሞዴልነት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መጀመራቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ማዕከላቱ ስር የሚገኙ የግብርና ምሁራንና ተመራማሪዎች አማካኝነት በአካባቢው በስንዴ ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች በግብዓት፣ በሙያና በቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማገዝ 700 ሄክታር መሬት መረከቡን ተናግረዋል፡፡
ዘመናዊ አሰራሮችንና ቴክሎጂዎችን የተከተለ የስንዴ ልማት በማካሄድ የክልሉን እቅድ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለስንዴ አልሚ አርሶ አደሮች የሙያ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለልማቱ የሚያስፈልገውን የዘር አቅርቦት ለመደገፍ በ320 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ሃላፊ አቶ አስፋው አዛናው ናቸው፡፡
ማዕከሉ ድርቅንና ተባይን እንዲሁም የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን በማእከላዊ፣ በምእራብና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የማላመድና የማስተዋወቅ ሥራ እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲከናወን በማድረግ ከ18 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
እስካሁን ከ154 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑንም ተገልጿል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.