Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በአፈር አሲዳማነት በየዓመቱ ከስንዴ ምርት 3 ቢሊየን የሚደርስ ብር  እንደሚታጣ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በአማራ ክልል በአፈር አሲዳማነት በየዓመቱ ከስንዴ ምርት ብቻ እስከ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ እንደሚታጣ ተገለጸ፡፡

በክልሉ አጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት 27 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አብዮት መኮንን ገልጸዋል፡፡

አቶ አብዮት በክልሉ ውስጥ በ9 ዞኖችና በ87 ወረዳዎች የሚገኙ 1 ሺህ 69 ቀበሌዎች ናቸው በአፈር አሲዳማነት መጠቃታቸውን የተናገሩት፡፡

ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሄረሰብ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በከፍተኛ ሁኔታ በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ ናቸው፤ ሰሜንና ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖችም ችግሩ መኖሩን ባለሙያው ገልፀውልናል። እነዚህ አካባቢዎች በአብዛኛው ተራራማና ተዳፋታማ በመሆናቸው መሬቱ በጎርፍ በመታጠቡ ለአፈር አሲዳማነት ችግር እንዲጋለጥ አድርጎታል ብለዋል፡፡

መሬት በተደጋጋሚ መታረስ፣ የሰብል ፈረቃ አለመኖር፣ ለመሬት የሚውል የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠን ዝቅተኛ መሆን፣ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ መሆንም ለአፈር አሲዳማነት መፈጠርና መባባስ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።

የአፈር አሲዳማነት ችግር ከ50 በመቶ እስከ መቶ በመቶ የሰብል ምርትን ይቀንሳል።

የክልሉ መንግሥት በችግሩ ስፋት ልክ መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉን ባለሙያው ገልጸው ለዚህ ደግሞ በመንግሥት በኩል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኖራው የሚገኝበት አካባቢ መራቅ የቀረበውን ኖራ በአግባቡ መጠቀም እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉም አንስተዋል፡፡

በእነዚህ ችግሮች ምክንያት በአፈር አሲዳማነት ከተጠቃው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ መመለስ የተቻለው ከ10 ሺህ ሄክታር አይበልጥም ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል።

በአፈር አሲዳማነት በተጠቃ መሬት በሄክታር ይገኝ ከነበረው 6 ኩንታል ምርት በኖራ በማከም እና ሌሎች ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ በመሥራት በሄክታር ከ80 እስከ 300  የምርት ጭማሪ ማምጣት መቻሉን ነው አቶ አብዮት የገለጹት፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.