Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ 991 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የዘይት ፋብሪካ የሙከራ ምርት ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ 991 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የዘይት ፋብሪካ የሙከራ ምርት መጀመሩን የኩባንያው ተወካይ ሥራ አስኪያጅ ዳዊት አውደው አስታወቁ።

ፋብሪካው በ80 በመቶ የመሥራት አቅሙ ማምረት ሲጀምር እስከ 1 ሚሊየን 500 ሺህ ኩንታል አኩሪ አተር በግብዓትነት ይጠቀማል ብለዋል።

ከዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆነውን ተጠቅሞ የአኩሪ አተር ፕሮቲን ዱቄት እንደሚያመርት የተገለፀ ሲሆን 1 ሚሊየን 200 ሺህ ኩንታል ዓመታዊ የፕሮቲን ዱቄት እንደሚያመርትም ገልፀዋል።

የአኩሪ አተር ፕሮቲኑ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ እና በዓመት 61 ሚሊየን 680 ሺህ ዶላር የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝም ተናግረዋል።

ከግብዓቱ 15 በመቶውን በመጠቀም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆን 22 ሚሊየን 500 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት እንደሚያመርት መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።

“ቀጣይ የአካባቢ ገበያ ጥናት የሚደረግ ቢሆንም አሁን ባለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ መሠረት አንድ ሊትር ዘይት በ 65 ብር ቢተመን እንኳን 1 ቢሊየን 462 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ገቢ ያስገኛልም” ነው ያሉት።

ቀሪው አምስት በመቶ የሚሆነው ምርት የእንስሳት መኖ መሆኑን በመግለፅ ይህም በዓመት 75 ሺህ ኩንታል የእንስሳት መኖ እንዲያመርት እንደሚያስችለውም አንስተዋል፡፡

በሙከራ ምርቱ ለ301 ሰዎች ቀጥታ የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከዚህ በላይ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተነግሯል።

የሙከራ ምርት ከጀመረው ፋብሪካ በተጨማሪ የበቆሎ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ 50 በመቶ መድረሱንም ተወካይ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.