Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ313 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን ከተፈናቀሉት ውስጥ እስካሁን ከ313 ሺህ በላይ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካበቢዎችም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚበልጥ ህዝብ ከቤት ንብረቱ በማፈናቀል ለከፋ ችግር እንዲጋለጥ ማድረጉን አስረድተዋል።

ከ7 ሚሊዮን የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ አካባቢያቸውን ሳይለቁ በሽብር ቡድኑ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው መቆየታቸውንም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን አካባቢዎቹ ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ በደብረ ብርሃን፣ ሞጣ፣ መካነ ሰላም፣ ባህር ዳር፣ እብናትን ጨምሮ በሰባት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድና ከህብረተሰቡ ጋር ተጠግተው የቆዩ ተፈናቃይ ወገኖች ወደቄያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስከሁን በተደረገው ጥረት 163 ሺህ ተፈናቃዮች መንግስት ትራንስፖርት በማመቻቸት፤ ከ150 ሺህ የሚበልጡት ደግሞ በራሳቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

የተመለሱትም በአብዛኛው መጠለያ ያላቸው ሲሆኑ የተጎዳባቸውም ባሉበት መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።

የቀሩ ተፈናቃዮችንም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደቀደመ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ እያሱ፥ ተመላሾች የዕለት ምግብ ይዘው እንዲሄዱም ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሰሜን ሸዋ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ህምራና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ወደ ቀያቸው ለተመለሱና ችግሩን ተቋቁመው በአካባቢያቸው ለቆዩ ወገኖችም 82 ሺህ 942 ኩንታል የዕለት ምግብ እህል በማከፋፈል ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ በተቋቋሙ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልለው ለቆዩ ወገኖችም እስካሁን 340 ሺህ ኩንታል የዕለት ምግብ እህል ድጋፍ በማድረግ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ ማሰራጨት መቻሉን አስታውሰዋል።

ህዝቡን መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ችግሩን ለመሻገር የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል ያሉት አቶ እያሱ፥ የመልሶ ማቋቋም ተግባሩን መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቱና ህብረተሰቡ በመደገፍ ርብርብ እንዲያደርጉም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.