Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪዎች የሕግ ማስከበር ተግባሩን በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪዎች መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር ተግባር እንደሚደግፉ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ጭምር የተሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፉ በዞኑ ሦስት ከተሞች በከሚሴ፣ ባቲና ጨፋ ሮቢት ነው የተካሄደው።

በሰልፉ ላይ “የሕግ ማስከበሩን ተግባር እንደግፋለን፣ ከመንግስት ጎንም እንቆማለን ፤ ሸኔ የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም ፤ አብሮነታችንን ለማስቀጠል ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ነን” የሚሉና ሌሎችም ሀሳቦች ተንጸባርቀዋል፡፡

በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ፥ በሕግ ማስከበር ተግባሩ ከ400 በላይ ከሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል፡፡

በዚህም በዞኑ አንፃራዊ ሰላም መፈጠሩን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፥ ሕግን ለማስከበር የክልሉ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና መከላከያ ሰራዊት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ማህበረሰቡም ከመንግስት ጋር ተሰልፎ ያሳየው አጋርነት የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የሸኔን ሕገወጥ ተግባራት የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

መንግስት ለሕግ የበላይነት መከበር እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ እና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ከመንግስት ጎን እንቆማለን ሲሉ ነዋሪዎቹ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል፡፡

“ሸኔ የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም” ያሉት የሰልፉ ተሳታፊዎች፥ ከመንግስት መዋቅር ውጭ የታጠቀ አካል የአካባቢያችንን ሰላም እንዲያውክ አንፈቅድም ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በሳምራዊት የስጋትና አለባቸው አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.