Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል 23 ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል የሚገኙ 23 ከተሞች በከተማ አስተዳደርነት እንዲመሩ መወሰኑን የክልሉ መንግስት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔውን ማስተላለፉ ተጠቁሟል።

በከተሞች የአደረጃጀት ፈርጅ መወሰኛና ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 65/2001 መሰረት መስፈርት አሟልተው የተገኙ 23 ከተሞች ከፈርጅ ሶስት ወደ ፈርጅ ሁለት የደረጃ ሽግግር ማለትም በከተማ አስተዳደርነት ለመመራት በክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ አጥንቶ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ምክር ቤቱ አጽድቋል ተብሏል፡፡

ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በስፋት መክሮ የከተሞችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመፍታትና ወደ ፊት ያላቸውን የመልማት ዕድል የተጠቀሱ ከተሞችን የደረጃ ሽግግር እንዳፀደቀው ተነግሯል ፡፡

በዚህም መሰረት ከደቡብ ጎንደር ዞን ወገዳ፣ ሀሙሲት እና እብናት፣ ከአዊ ብሄረሰብ ዞን አዲስ ቅዳም፣አገው ግምጃ ቤት፣ ፈንድቃ፣ ከምስራቅ ጐጃም ዞን ደብረ ወርቅ፣ ሉማሜ፣ አማኑኤል እና ግንደ ወይን፣ ከምዕራብ ጐጃም ዞን ሽንዲ እና ጅጋ ከተሞች ይገኙበታል ፡፡

ከደቡብ ወሎ ዞን ከላላ፣ ቱሉ አውሊያ፣ ሀርቡ፣ አቀስታ፣ ደጎሎ፣ ከሰሜን ሽዋ ዞን ደብረሲና፣ ሞላሌ፣ እነዋሪ፣ ከሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና እንዲሁም ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደግሞ ቆላድባ እና ሻውራ የከተማ መስፈርቱን ያሟሉ ሆነው በመገኘታቸው በከተማ አስተዳደር እንዲመሩ ተወስኗል፡፡

በመሆኑም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የተጠቀሱት ከተሞች ከፈርጅ ሶስት ወደ ፈርጅ ሁለት የደረጃ ሽግግር በማድረግ የከተማ አስተዳደርነት ዕውቅና እንዲያገኙ የክልሉ ምክር ቤት እንደወሰነ ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡

ተግባራዊነቱን በተመለከተም ክልሉ ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የበጀት እጥረት ያጋጠመ በመሆኑ የደረጃ ሽግግር የተፈቀደላቸው 23ቱ ከተሞች ከክልል የስራ ማስኬጃም ይሁን ሌላ በጀት የማይመደብ መሆኑን አውቀው በራሳቸው በጀት ቁጠባን መሰረት በማድረግ ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸውም አስታውቋል፡፡

ተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.