Fana: At a Speed of Life!

በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ብሄራዊ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃ ማዕከል የዲጂታል ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ብሄራዊ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃ ማዕከል የዲጂታል አሰራር ተመርቆ ስራ ጀመረ።

ማዕከሉ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ፥ አዲሱን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ጨምሮ ኮቪድ-19፣ ቢጫ ወባ፣ ኮሌራ እና ጊኒ ወርም ዙሪያ የህብረተሰብ ጤና መረጃዎችን የሚሰጥ ነው።

8335 ላይ ነፃ አገልግሎት የሚሰጠው ብሔራዊ የህብረተሰብ ጤና ስጋት መረጃ ማዕከሉ አስተማማኝ የቀድሞ ማስጠንቀቅ፣ የምርመራና የክትትል መረጃዎችን ይሰጣል።

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ፥ የዲጂታል አገልግሎት ሥርዓቱ ጊዜውን የጠበቀ፣ አስተማማኝ የህብረተሰብ ጤና መረጃ በመስጠትና ጥቆማዎችን በመቀበል ኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሻሽል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ፥ የዲጂታል አገልግሎቱ በርካታ ደንበኞችን በአንድ ጊዜ ማስተናገዱ፣ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አውቶሜትድ ማድረጉ፣ ጥቆማዎችን መቀበል ማስቻሉና በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠቱ የጤናውን ዘርፍ ዲጂታላይዜሽን ያሻሽለዋል ብለዋል።

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ያለው ፥ ከዚህ ዲጂታል ፕላትፎርም የሚገኙት ትምህርቶች የተለያዩ ዘርፎች ላይ ለሚሰራው የዲጂታል ሥራ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዲጂታል ፕላትፎርሙ ድምጽና የጽሁፍ መልዕክትን አቀናጅቶ የሚጠቀምና በተለይም ደግሞ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች በሚፈጠሩባቸው አስቸኳይ ጊዜያት ብዛት ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያዳርስ መሆኑን ከሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.