Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪው ህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ጎራ ለይተው የተሰለፉ ታጣቂዎች እርስ በእርስ ተገዳደሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ጎራ ለይተው የተሰለፉ ታጣቂዎች እርስ በእርስ መገዳደላቸው የመረጃ ምንጮች አረጋገጡ።
ሰርጎ በገባባቸው የተለያዩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ሽንፈት አጋጥሞት እየተበታተነ በሚገኘው የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አመራሮች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ጎራ ለይተው የተሰለፉ ታጣቂዎች እርስ በእርስ መገዳደላቸው እና የተወሰኑትም ከቡድኑ ተነጥለው መሄዳቸውን ነው ታማኝ ምንጮች ያረጋገጡት፡፡
የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ሰሞኑን በሁሉም ግንባሮች የደረሰባቸውን ሽንፈት ተከትሎ በምዕራብ ግንባር ከተለያዩ ስፍራዎች የተራረፉ ታጣቂዎችን እንደገና ለማደራጀት ሙከራ ባደረጉበት ስብሰባ፥ ብዙዎች የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላቸውና አላማ ለሌለው ጦርነት ዋጋ መክፈል እንደማይፈልጉ በመግለጻቸው አለመግባባት መፍጠሩን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ስብሰባው በአመራሮችም መካከል ከፍተኛ ንትርክና ጭቅጭቅ ያስተናገደ እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ፥ በተለያየ ጎራ በተሰለፉ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት አስር ሰዎች መሞታቸውና ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ስብሰባውን አቋርጠው መሄዳቸው ታውቋል፡፡
ምንጮቻችን እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ በገባባቸው የወልዲያና የሰቆጣ አካባቢዎችም ከፍተኛ የተዋጊ ሃይል እጥረት ስላጋጠመው የአካባቢውን ወጣቶች በግዳጅ ወደ ጦርነት ለማስገባት እየሞከረ መሆኑንም ገልጸውልናል።
ሃሳቡ ያልተሳካለት አሸባሪ ቡድኑ በወጣቶች እንዲሁም በወላጆች ላይ እርምጃ እንወስዳለን በማለት እያስፈራራ ቢሆንም፥ በተቃራኒው በተደራጀ መንገድ ምከታ እየገጠመው መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ ሰሞኑን በጠለምት የአካባቢው  ሚሊሻዎችና ነዋሪዎች በተደራጀ መንገድ የአሸባሪ ቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግታት የቻሉ ሲሆን፥ 300 የሚደርሱ የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎችም ተደምስሰዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.