Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል በበረሃሌ ጣቢያ የነበሩ ከ34 ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞች ተፈናቅለዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በፈጸመው ዳግም ወረራ በበረሃሌ የስደተኞች ጣቢያ የነበሩ 34 ሺህ 246 የኤርትራ ስደተኞች መፈናቀላቸውን ከስደት ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ።

አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን በፈጸመው ዳግም ወረራ በበረሃሌ የስደተኞች ጣቢያ የነበሩ 34 ሺህ 246 የኤርትራ ስደተኞች ከነበሩበት ካምፕ መፈናቀላቸውን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት የሰመራ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ቡድኑ በስደተኛ ካምፑ ላይ በከፈተው የከባድ መሳሪያ ጥቃትም አምስት ስደተኞች መገደላቸውንና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል።

የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ጋሻው እንደገለጹት÷ አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ላይ ዳግም ወረራ በፈፀመበት ወቅት በዚሁ ስፍራ የሚገኘው የበረሃሌ የስደተኞች ካምፕ አንዱ የጥቃቱ ዒላማ ስለነበር ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበታል።

አሸባሪው ህወሓት በካምፑ ላይ በከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈፀም በካምፑ ውስጥ የነበሩ ስደተኞችን ለዳግም መፈናቀል መዳረጉንና መጠለያ ካምፖችንም የጦር መሳሪያ ማከማቻ ማድረጉን ተናግረዋል።

ቡድኑ በእነዚህ ስደተኞች ላይ የፈፀመው ጥቃት የዓለም አቀፉን የስደተኞች መርህ የሚጣረስ ነው ያሉት አቶ ፋሲል÷ አንድ ወታደር አልያም የታጠቀ ኃይል በስፍራው በሌለበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ጥቃት መፈፀሙ አሳዛኝ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትም በሚገባው ልክ እየደገፉ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ስደተኞቹ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መንግሥት ከአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እኩል የሚችለውን ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛልም ነው ያሉት።

የተፈናቀሉ ስደተኞችን በአንድ ቦታ በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ በሰርዶ አካባቢ የስደተኞች ካምፕ እየተዘጋጀ መሆኑንና በሳምንት ጊዜ ውስጥ በአንድ አካባቢ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ነው የተናገሩት፡፡

ከበረሃሌ ስደተኞች ካምፕ ተፈናቅለው በሠመራ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች÷ አሸባሪው ቡድን ዳግም ወረራ በፈጸመበት ወቅት እነሱን መሰረት ያደረገ የከባድ መሳሪያ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

ቡድኑ በስደተኞቹ ካምፕ ላይ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈጽሞ ለከፋ ጉዳት እንደዳረጋቸው ከበረሃሌ የስደተኞች ጣቢያ የተፈናቀሉ ወገኖች ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በካምፑ ላይ በከፈተው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውንና ከፊሎቹ አቅጣጫ በመሳት ወደኋላ የተመለሱና በሽብር ቡድኑ ተቆርጠው የቀሩ እንዳሉ ተፈናቃዮች ለኢፕድ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በ25 የስደተኛ ጣቢያዎች ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን÷ በአፋር ክልል በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች 61 ሺህ 200 የኤርትራ ስደተኞች ይገኛሉ፡፡

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.