Fana: At a Speed of Life!

በአብሮነት፣ በሀይማኖትና ብዝሃነት ላይ ያተኮረ ምክክር በሀረር ከተማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰላም በአብሮነት፣ በሀይማኖትና ብዝሃነት ላይ ያተኮረ ምክክር የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀረር ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ በእንግድነት የተገኙት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የምክክር መድረኩ በሀረር ከተማ መካሄዱ ከተማዋ እና ነዋሪዎቿ የሚታወቁበት ሐይማኖታዊና ማህበራዊ እሴቶችን ለማጠናከርና ተሞክሮ ለመቀመርና ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋት መልካም እድል ይፈጥራል ብለዋል።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በማረም ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ወደ ቀደመ ታላቅነት የሚያሸጋግሩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገሪቱ ፅንፈኝነትን በመከላከል ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት እንዲሁም ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ይህን ተግባር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ በበኩላቸው የሀይማኖት ተቋማት ዜጎችን በማስተማርና በማነፅ በሰላም እና በመከባበር እንዲኖሩ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃርም የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተመሰረተበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።

ግጭት ሳይፈጠር አስቀድሞ መከላከል ላይ አተኩሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ጸሀፊው የሀይማኖት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት የዜጎችን የመተባበርና የአንድነት እሴት ማስቀጠል እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የሀረሪ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መጋቢ መስፍን በየነ ለተጋመዱና ለተሳሰሩ እሴቶች ዋጋ መስጠት አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ከሀረሪ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአውደ ምህረቶችና በመስጂዶች ከምንጊዜውም በላይ ሰላምና አብሮነትን በመስበክና በማስተማር ህዝቡ በተለይም ወጣቱ የሰላም አምባሳደር እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ በዚህ ወቅት ተነስቷል።

ለሁለት ቀናት በሚደረገው የምክክር መድረክ ሰላምና አብሮነት እንዲሁም የሃይማኖትና የብሔር ብዝሃነት አያያዝ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የውይይት ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.