Fana: At a Speed of Life!

በአቶ በቀለ ገርባ ላይ በቂ ምርመራ ማድረጉንና የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ መከፈቱን መርማሪ ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦፌኮ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በዛሬው እለት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።

በዚህም አቶ በቀለ ገርባ የእርስ በእርስ ግጭት ወንጀል በማነሳሳት የተጠረጠሩ መሆናቸውን ተከትሎ መርማሪ ፖሊስ በቂ ምርመራ ማድረጉን በመግለፅ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ መክፈቱን ለችሎቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ አቶ በቀለ በአዲስ አበባ እና በአካባቢው እንዲሁም በሻሸመኔ ባስተላለፉት ትእዛዝ በተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ በትራንስፖርት ዘርፉ ብቻ በመንግስት 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር፤ በግል ደግሞ 29 ነጥን 8 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የሚያመላክት 45 ገፅ ሰነድ ማሰባሰቡን ጠቅሷል።

በተጨማሪም 27 ምስክሮችን መቀበሉን የገለፀው መርማሪ ፖሊስ፥ በሻሸመኔ እና አካባቢው በተነሳው ብሄር ተኮርና ሀይማኖት ተኮር ግጭት የ32 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ 110 ሆቴሎች መቃጠላቸውን፣ 239 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ 393 መኖሪያ ቤቶች የተዘረፉ መሆናቸውን፣ 56 ሱቆች የተቃጠሉ መሆናቸውን፥ 146 ሱቆች የተዘረፉ መሆናቸውን፣ 80 የግል ተሽከርካሪ መቃጠላቸውን፣ 1 ፋብሪካና 9 ወፍጮ ቤቶች መቃጠላቸውን 63 የግል ድርጅቶች መቃጠላቸውን፣ 42 ባጃጆች፣ 18 ሞተር ሳይክሎች የተቃጠሉ ሲሆን፥ 4 ባንኮች እና 2 የብድርና ቁጠባ ተቋማት መቃጠላቸውን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።

እንዲሁም 1 ሺህ 128 ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።

በተጨማሪም 7 ሽጉጦች መገኘታቸውንና 2 ሽጉጦች በአቶ በቀለ ገርባ እጅ የተገኙ መሆናቸውን እና ህገ ወጥ መሆናቸውን በፎረንሲክ ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በቡራዩ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን እንዳያልፍ መንገድ እንዲዘጋ አስቀድመው ትእዛዝ መስጠታቸውን እና አስከሬን ወደ አዲስ አበባ በመመለስ 10 ቀን መስቀል አደባባይ በማቆየት፣ የሚኒሊክ ሀውልትን ለማፍረስና ቤተ መንግስት በመግባት ጥቃት ለመፈፀም እቅድ ይዘው በኦሮሚያ ብልፅግና ጽህፈት ቤት አስክሬን በሀይል ማስገባታቸውንና በዚህ ወቅትም በፀጥታ ሀይል ላይ ተኩስ በመክፈት አንዱ ህይወቱ ሲያልፍ 3 ጉዳት አንደደረሰባቸው በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።

አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው፥ “እኔን አስሮ ከምርጫው ለማግለል ታስቦ ነው፤ የፖለቲካ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዳለኝ ስለሚታወቅ እንጂ እኔ በወንጀሉ ተሳታፊ አይደለሁም” ብለው ተከራክረዋል።

ከሽጉጦቹ ጋር በተያያዘም እንደ አጠቃላይ የተያዙ በመሆናቸው እኔን አይመለከትም “ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ይህንን አውቆ በዋስትና እንድለቀቅ እንዲፈቅድልኝ” ሲሉ ጠይቀዋል።

ጠበቆቻቸውም በበኩላቸው፥ ምርመራው ከደንበኛቸው ጋር እንደማይገናኝ እና የደንበኛቸውን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ፍርድ ቤቱ በዋስ እንዲለቃቸው ጠይቀዋል።

አቶ በቀለ ምንም ባላደረጉት ተሳትፎ ነው ምርመራው የሚደረገው፤ በአጠቃላይ በተፈፀመው ድርጊት ሊጠየቁ አይገባም ሲሉም ተቃውመው ተከራክረዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ በቂ ምርመራ ማድረጉን በመጥቀስ፥ አቶ በቀለ ገርባ ባስተላለፉት ትእዛዝ የደረሰ የንብረት መውደም እና የሰው ህይወት መጥፋት መሆኑንም ምርመራው ያመላክታክል፤ ይሁን እና ይህ የምርመራ መዝገብ ተዘግቶ አቃቤ ህግ
የከፈተው የቀዳሚ የምርመራ መዝገብ እንዲቀጥል ይፈቀድ ሲል ጠይቋል።

አቃቤ ህግም በዚህ መዝገብ ላይ ቀርቦ ምላሽ ሰጥቷል፤ በመዝገብ ቁጥር 215585 የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ መክፈቱን ገልጿል።

በዚህም የምርመራ መዝገብ ተጠርጣሪው የእርስ በእርስ ወንጀል በማነሳሳት የተጠረጠረ በመሆኑ በወንጀል ህጉ 240 መሰረት ሊከሰሱ እንደሚችሉ ቀዳሚ ምርመራው አመላካች መሆኑን ጠቅሷል።

ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ የሰው ህይወት ያለፈበት ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቦ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ሽጉጥን በተመለከተ በአቶ በቀለ ላይ የተገኙት ሁለቱም ተነጥሎ በድርሻቸው የቀረበ በመሆኑ መዝገቡ እንዲዘጋ ሲልም አቃቤ ህግ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆችም የቅድመ ምርመራ መዝገቡ የሰው ምስክርን ተጠባባቂ ለማድረግ የሚሰራ ነው፤ በዚህ መዝገብ የሚያስጠረጥራቸው ተግባር አለ ወይ የሚለው ይለይልን ሲሉም ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በነገው እለት እንዲቀርብለት አዟል።

ዋስትናን በተመለከተ ለመስጠት ለሀምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.