Fana: At a Speed of Life!

በአንድ ሳምንት ውስጥ 319 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድ ሳምንት ውስጥ 319 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ትግራይ ክልል መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።
ሰብዓዊ እርዳታ ዳግም ወደ ክልሉ መግባት ከጀመረበት መጋቢት 23 ቀን ጀምሮም በአጠቃላይ 571 ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባታቸውን ቢሮው ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
ከዚህ ቀን ጀምሮም በ46 ቀናት ውስጥ 15 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን ምግብ ወድ ክልሉ ተልኳል ብሏል።
ይሁን እንጅ በክልሉ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ 68 ሺህ ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በትዊተር ገጹ ያወጣው ሪፖርት ያመላክታል።
ቢሮው አያይዞም ከአዲስ አበባ መቐለ በየሳምነቱ ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች እንደሚደረጉ ጠቅሶ፥ በአምስት ወራት ውስጥ በአጋር ተቋማት በኩል 711 ነጥብ 6 ሜትሪክ ቶን ሰብዓዊ እርዳታ መጓጓዙን አመላክቷል።
ከትግራይ ባለፈ በአማራ እና አፋር ክልሎችም ተመሳሳይ የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አስታውሷል።

በዚህም በአማራ ክልል በግንቦት ወር መጀመሪያ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ 21 ሺህ 300 ህጻናት እና 14 ሺህ 200 ነፍሰ ጡሮች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማድረጉንም ነው ያስታወቀው።

በተጨማሪም በአፋር ክልል ለ100 ሺህ ሰዎች በቦቴ ውሃ ማቅረብ መቻሉንም ጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.