Fana: At a Speed of Life!

በአውሮፓ በኮቪድ ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት አንጻር 40 በመቶ ጨመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአውሮፓ በኮቪድ ምክንያት በየዕለቱ ለህልፈት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት አንጻር ሲታይ 40 በመቶ ገደማ መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስ እንደገለጹት በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በብሪታንያ፣ በኔዘርላንድስ እና በሩሲያ በዋናነት ወረርሽኙ ስር የሰደደባቸው ሃገራት ናቸው፡፡

ቃል አቀባይዋ የፅኑ ህሙማን ማዕከሎች በህሙማን እየተጨናነቁ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሩሲያ 320፣ በስፔን 221፣ በፈረንሳይ 523 እና በኦስትሪያ 1 ሺህ ሰዎች ለህለፈት ተዳርገዋል፡፡

በፈረንሳይ ትናንት የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ከሚያዝያ ወር በኋላ የከፋው ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በሩሲያ ከ16 ሺህ በላይ፣ በፈረንሳይ ከ33 ሺህ ሰው በላይ እንዲሁም በጣልያን 22 ሺህ ሰዎች መያዛቸው ተመዝግቧል፡፡

ወረርሽኙ እየተባባሰባቸው ከሚገኙ ሃገራት መካከል በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሩሲያ ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲደረግ ወስናለች፡፡

በሌላ በኩል በጣልያን የተላለፈውን ክልከላ ተከትሎ በሚላን፣ በቱሪን እና በሌሎች ከተሞች ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

በአውሮፓ ዳግም የተቀሰቀሰው ወረርሽኝ ምናልባትም መጀመሪያ ከተከሰተው የባሰ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.