Fana: At a Speed of Life!

በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ 233 ሺህ 557 ዶላር ስጦታና ቦንድ ግዥ ፈጸሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን 233 ሺህ 557 የአሜሪካ ዶላር በስጦታና በቦንድ ግዥ ፈፀሙ።

“ግድቡ እንዲጠናቀቅ የበኩሌን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ፤ ለትውልድ አሻራዬን አስቀምጣለሁ” በሚል መሪ ቃል ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ የሚውል የገንዘብ አስተዋፅዖ ለማበርከት በሀገራቱ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የታደሙበት የቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የኢፌደሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋችው ባስተላለፉት መልዕክት የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት ለማስመስከር አስተዋፅዖ ማድረጉን ገልጸዋል።

አቶ ገዱ በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታና እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በተደረገው ጥረት ዳያስፖራው እይደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስገናቸውን አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በማያያዝም ግድቡ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላት ሉዓላዊ መብት በምንም የሚተካ አለመሆኑን እና ግድቡን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአውስትራሊያና በኒውዝላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ቦንድ በመግዛት፣ በዕውቀታቸው፣ የኢትዮጵያን አቋም ለሚመለክታቸው እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በማስረዳት የሚችሉትን ሁሉ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.