Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ ዓመት የህግ የበላይነት በማስከበር የዜጎችን ደንህነት ለማረጋገጥ አጥብቆ እንደሚሰራ የብልፅግና ፓርቲ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 2013 ዓ.ም ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት እና ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የሀገሪቱ አቅጣጫ ሄደው ሃብት የሚያፈሩበት ለማድረግ እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።

የፓርቲው የውጭ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በተጠናቀቀው ዓመት የብልጽግና ፓርቲ አለም አቀፍና ሃገራዊ ፈተናዎቹን አልፎ ድንቅ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዞ ከአዙሪት በማውጣትና ከአንባገነን ስርዓት በማላቀቅ በአዲስ ተስፋ ላይ መሰረቱን የጣለበት ዓመት ነው ብለዋል።

በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ተበታትኖ የቆየውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ወደ አንድነት በማምጣት በይቅርታ፣ በመደመር፣ በአንድነት መንፈስ አብሮ የመጓዝን ጮራ ፈንጥቋል ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ ባለፉት 28 ዓመታት ብሄርን መሰረት አድረገው ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ውጤታማ ስራዎች ቢሰሩም የዚያኑ ያክል በሃገራዊ አብሮነት እና አንድነት ላይ ስራ ችላ በመባሉ የጽንፈኝነት ጽንስ እንዲፋፋ እና እንዲወለድ አድረጓል ነው ያሉት።

የለውጥ ጉዞውን ለመጎተት የሞከሩ የብሄርና የሃይማኖትን ፅንፈኝነት ያስከተሉት መፈናቀልና ጉዳት መከሰቱን ጠቁመው፤ በለውጡ የተመዘገቡ ድንቅ ስኬቶችን ለማደብዘዝ መሞከራቸውን አንስተዋል።

በለውጡ የተመዘገቡ ድንቅ ስኬቶችን ለማደብዘዝ የሞከሩ ፈተናዎችን እስከወዲያኛው ለማስቀረት በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ አንድነትን ማፅናት የፓርቲው የአዲሱ ዓመት የቤት ስራ መሆኑ ተናግራዋል።

ከዚያም ባለፈ በኢትዮጵያ የብሄርም ይሁን የሃይማኖት ጽንፈኝነት ትልቅ አደጋ መሆኑን የተገነዘብንበት ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራትም ይጠበቅበናል ብለዋል።

ስለሆነም ፓርቲው አዲሱን ዓመት እነዚህ ችግሮች ከመቅረፍ ባሻገርም ህዝቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የመፍቻ ዓመት አድርጎ እንደሚሰራ ሃላፊው ተናግረዋል።

ሃላፊው አያይዘውም የተረጋጋና ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ገባዋልም ነው ያሉት።

በበላይ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.