Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ለገና በዓል ለ50 ሺህ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ለ50 ሺህ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ድጋፍ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍስሀ ጥበቡ ለበዓሉ የሚደረገው ድጋፍ “አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ” በሚል የተጀመረው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብርና የበጋ በጎ ፈቃድ ሥራዎች አካል ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ለአቅመ ደካሞች የሚደረገው ድጋፍ እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕልን በማዳበር የሚገኘውን ደስታ ሙሉ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አቶ ፍስሃ ገልፀዋል።

ከሠብዓዊ ድጋፉ ባሻገር የገናን በዓልን ምክንያት በማድረግ 187 የአረጋዊያን መኖሪያ ቤቶችን የማደስ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ቤታቸው የታደሰላቸው የአገር ባለውለታ አረጋዊያን ጧሪና ደጋፊ በማጣት ቤታቸውን ማደስ ያልቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“በገና ስጦታ የሚበረከትላቸው ሠብዓዊ ድጋፍ በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አስተባባሪነት ለሚደረገው ሠብዓዊ ድጋፍ የከተማዋ ነዋሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም አክለዋል።

በአይነት የሚደረገው ድጋፍ ለበዓል የሚሆኑ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ እንደሚያካትት ጠቁመዋል።

ለአረጋዊያኑና ለአቅመ ደካሞቹ ከእርድ እንስሳት ውጭ የሚደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆንም ምክትል የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል።

ቢሮው 50 ሺህ ለሚሆኑ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የእንኳን አደረሳችሁ የገና በዓል ስጦታ ለማበርከት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ፍስሃ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.