Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ ለሚያገለግሉ ሠራተኞች የበዓል ስጦታ ተበረከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ንኡስ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ቦታ የተለያዩ አገልግሎት ለሚሰጡ ሠራተኞች የበዓል ስጦታ አበረከተ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ትላንት ማምሻውን በቦታው ተገኝተው ሠራተኞቹን ለሚያደርጉት ጥረት አመስግነዋል።

ኃላፊዎቹ በዚህ ወቅት 1 ሺህ 441ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ስምንት በግና ፍየሎችን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ባሉበት አስረክበዋል።

የበዓል ስጦታው በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በማገልገል ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ የጸጥታ ሰራተኞች፣ የፅዳት ሰራተኞችና በተያያዥ ሙያ ለተሰማሩ የተበረከተ ነው።

ሠራተኞቹ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ሥራ ላይ እየሰጡ ላሉት አገልግሎት ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

ሰራተኞቹ ለሚሰጡት አገልግሎት መንግስት ከጎናቸው እንደሆነ የገለጹት ኃላፊዎቹ፤ በቀጣይም ለአገራቸው እየከፈሉት ያለውን መስዋዕትነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.