Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸውንና ህገወጦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተወሰደ  እርምጃ  በርካታ ህገወጥ መሳሪያዎችና ሰነዶች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸውንና ሌሎች ህገወጦችን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል እየተወሰደ ባለው እርምጃ አሁንም በርካታ ህገወጥ መሳሪያዎችና የተለያዩ ሰነዶች እየተያዙ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በደረሰው ጥቆማ በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ኤድናሞል ህንፃ ስር በሚገኝ በአንድ ግለሰብ መጋዘን ውስጥ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 21 የሬዲዮ መገናኛዎች፣ በቤተ መንግስት ብቻ የሚገኝ አንድ ጋሻ፣ አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 መሰል ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።

በተመሳሳይ በዚሁ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አትላስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሌላ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ አንድ ሽጉጥ ከመሰል ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቀበሌ 19 በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ፍተሻ በህገ ወጥ መንገድ የተዘጋጁ 18 የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች፣ 3 የልደት ካርዶች፣ 13 የስራ ልምዶች፣ 10 የህክምና ማስረጃዎች፣ 22 የወሳኝ ኩነት መሸኛዎች፣ 6 የተለያዩ የባንክ ደብተሮች፣ 7 የተለያዩ የቀበሌ መታወቂያዎች፣ አንድ ካሜራ፣ 4 ማህተም እና አንድ የከበረ ድንጋይ የተገኘ ሲሆን፥ ግለሰቡም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ነው ምንጮቻችን የገለፁልን።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.