Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የ100 ሺህ ዩሮ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የ100 ሺህ ዩሮ ድጋፍ አደረገ።

የተደረገው ድጋፍ የምክር ቤቱ አባላት ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባር አክብረው መስራት የሚችሉበትን የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚውል መሆኑም ታውቋል።

የምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በህግና በስነምግባር ብቻ ተመርተው እንዲያከናውኑ ይሰራል ብሏል።

በስራ ሂደት የሚፈጠር ክፍተትን ራሳቸውን በራሳቸው የሚያርሙበት የግልግል ዳኝነት አካል አቋቁሞ ስራ ለመጀመር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛልም ብሏል።

ይህንኑ መሠረት በማድረግ ሚዲያዎች ከፍርድ ቤት በመለስ በፈቃደኝነት የሚዳኙበት ሥርዓትን ለማጠናከርና የምክር ቤቱን አባላት ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባር አክብረው መስራት የሚችሉበትን የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚውል የፕሮጀክት በጀት በአዲስ አበባ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ የ100 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ተደርጎለታል።

በዛሬው እለት ድጋፉ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሚስተር ሬሚ ማሬሾ እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ ተፈርሟል።

የበጀት ድጋፉ በምክር ቤቱ በቀረበው የፕሮጀክት እቅድ መሠረት የሚፈፀም ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሚስተር ሬሚ ማሬሾ በስነ ስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ሚዲያ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሠረት ነው።

በመሆኑም መንግስታቸው ነፃና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ እንዲጠናከር ፍላጎቱ እንደሆነ ገልፀው በቀጣይነትም ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው የምክር ቤቱ የስራ ማስኬጃ በአባላት መዋጮ የሚሸፈን መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ ያደራጀው የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት አካል እንዲጠናከር እንዲሁም የስነ ምግባር ደንቡን በጋዜጠኞች ውስጥ ለማስረፅ ለተቀረፀው ፕሮጀክት የፈረንሳይ ኤምባሲ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

መገናኛ ብዙሃን ራሳቸውን በራሳቸው የሚዳኙበትን ስርዓት በመመስረት ሙያዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለውን የስነ ምግባር ችግሮች ለመቀነስና ራስን በራስ የመዳኘት ባህልን ለማሳደግ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.