Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በጋር ለመስራት የስምምነት ሰነድ ፈረሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በትምህርት፣ በሥልጠናና በአቅም ግንባታ ዘርፍ ተባብረው ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተገለፀ።

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ፣ ከአገርና ከህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እና የተጀመረውን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትምህርት ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ሙያዊ ክህሎትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመሥራት ከስምምነት ላይ ደርሷል።

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እና የብሔራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሀላፊ አቶ ወንድወሰን ካሳ ተፈራርመዋል፡፡

በዚህም ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴሚናሮችን፣ ጉባኤዎችን፣ወርክ ሾፖችንና ፐብሊክ ሌክቸሮችን በጋራ ለማዘጋጀት፤ የጥናትና ምርምር ውጤቶችንና የተለያዩ ህትመቶችን ለመለዋወጥ እንዲሁም በሰው ሃይል አቅም ግንባታና በስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ዙሪያ ተባብረው ለመሥራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ጋርም በአጋርነት የሚሰራበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ፕሮፌሰር ጣሰው በስምምነቱ ወቅት ማረጋገጣቸውን ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

በስምምነቱ መሠረትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ለብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አመራሮች እና ሠራተኞች በመደበኛ ፣ በርቀትና በተከታታይ በቅድመ ምርቃ እንዲሁም በድህረ ምርቃ መርሃ ግብሮች የትምህርትና ሥልጠና እድሎችን ለመስጠት መስማማቱ ተገልጿል።

ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የትምህርት መርሃ ግብሮቹን በከፍተኛ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ አሰገምግሞ በዲፕሎማ እና በዲግሪ መርሃግብሮች ትምህርትና ሌሎች ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችለውን እውቅና ባለፈው አመት ማግኘቱን ተቋሙ በላከልን መረጃ አስታውሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.