Fana: At a Speed of Life!

በአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች በነበረው የፀጥታ ችግር በወንጀሉ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን በመለየት ለፍርድ እንደሚያቀርብ በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ የፀጥታ ሃይሉ በአካባቢው የነበረውን የፀጥታ ችግር ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በነበረው ችግር ተዘግቶ የነበረውን መንገድ በማስከፈት የተቋረጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ሥራዎች እንዲጀመሩ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስና በወንጀሉ መጠየቅ ያለባቸውን አካላት በመለየት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሌተናል ጄኔራል ደስታ ተናግረዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ “በአካባቢው መረጋጋት በመፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶችና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል” ብለዋል።
የስልክ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩንም ሌተናል ጄኔራል ደስታ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና አምስት ከተሞች ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ የሚታወስ ነው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.