Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል መጤ አረምን በመጠቀም ኃይል ማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል እየተስፋፋ የመጣውን መጤ አረም (ፕሮሶፊስ ጁሊፌራን) በመጠቀም ኃይል ማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡
መጤ አረሙን በመጠቀም ኃይል (ባዮ ማስ) ማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት በክልሉ አሚባራ ወረዳ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይም÷ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ እና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በአፋር ክልል ብቻ÷ በመጤ አረሙ ምክንያት በዓመት ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃ እንደሚባክንና በዚህም ድርቅ እንዲከሰት ስለማድረጉ ተመላክቷል፡፡
የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ምርምር ማዕከል የአካባቢ ጥበቃ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክተር ዳዊት ዓለሙ እንደገለጹት÷ ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በፈረንጆቹ ከ2015 ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በአፋርና ሶማሌ ክልሎች 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ አረሙ መከሰቱን ጠቁመው÷ አረሙን በማንሳትና በማቃጠል የኃይል ተጠቃሚ ለመሆን እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከኃይል ተጠቃሚነት ባለፈ÷ አረሙን በማጽዳት መሬቱ ለምርት አገልግሎት እንዲውል የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ለፋብሪካዎች ግብአት የሚሆን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት ከ300 እስከ 400 ሚሊየን ዶላር ድረስ ወጪ እንደምታደርግ ጠቁመው÷ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ብቻ በየዓመቱ 1 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል እንደሚጠቀሙ አብራርተዋል፡፡
ከፕሮጀክቱ በሚገኘው ኃይል ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል እስከ 40 በመቶ ለመተካት ግብ ተይዟል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በ1970 ዓ.ም አካባቢ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተብሎ ወደ አገር ውስጥ የገባው መጤ አረም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች በመስፋፋት ምርታማነት እያሳጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት÷ አንድ የመጤ አረም ተክል በአማካይ በቀን እስከ 7 ሊትር ውሃ ከመሬት ውስጥ የመምጠጥ አቅም አለው።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.