Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል ከህግ ውጪ በሆን መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ200 በላይ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ  ህይወት ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ከህግ ውጪ በሆን መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ200 በላይ ታጣቂ ሃይሎች የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የኢፌዴሪ ሃገር መከላከያ ሰራዊት ባደረጉት ጥረት ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመለሱ፡፡

ታጣቂዎቹ የተጀመረው የሰላም አማራጭ በቀጣይ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሁለት አመት በፊት የተፈጠረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ የተለያዩ ሃይሎች በተላለፈው ጥሪ መሰረት በኤርትራ ቆላማ አካባቢዎች ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (እጉጉሞ) ከ300 በላይ ታጣቂ ሀይሎች ባለፈው አመት ሰላማዊ ትግልን መርጠው ወደ አገራቸው መግባታቸው ይታወሳል፡፡

ሰላማዊና ህጋዊ መንገድን መርጠው ወደ አገር ውስጥ ገብተው ከነበሩት የታጣቂ ቡድኑ አባላት የተወሰኑት በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ከማቆያ ካምፕ በመውጣት እንደገና ወደ ቀድሞ የታጣቂነት ሕይወታቸው ተመልሰው እንደነበር ነው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የጠቆመው፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢፌዲሪ ሃገር መከላከያ ጋር በመሆን  የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በማለም ታጣቂዎቹ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በጥብቅ ሙያዊ ሚስጥርና ስነምግባር የመረጃ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውንም አመልክቷል፡፡

ይህን ተከትሎም ከ35 ዲግሪ እስክ 43 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሞቃታማ የአየር ሁኔታ በሚስተዋልበት፤መልካ ምድራዊ አቀማመጡም በአብዛኛው ተራራማና ድንጋያማ በሆነባቸው ቆላማ አካባቢዎች የነበሩ ከ200 በላይ የሚሆኑ እነዚህ ታጣቂ ሃይሎች ከክልሉ መንግስት፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከጎሳ መሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ ሃይሎች በቀጣይ ከነፍጥ ይልቅ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ማረጋገጣቸውን አስታውቋል።

ታጣቂዎቹም ቃል በገቡት መሠረት ከክልሉ መንግስትና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በቀጣይ በክልሉ እንዲሁም በሀገር ሰላምና ደህንነት ግንባታ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ  ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ወቅትም ታጣቂ ሃይሎቹ የተለያዩ የተሃድሶና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ወስደው፤ በሰላም ሚንስቴርና በክልሉ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ቀጣይ ሰላማዊ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ ተመቻችቷላቸው ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን አገልግሎቱ አስታውቋል።

የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተቀላቀሉት የአሁኖችንና ባለፈው አመት የገቡትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ500 በላይ መሆናቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.