Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ 49 ሺህ 65 ሰዎች ተጠቅተዋል

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ 49 ሺህ 65 ሰዎች መጠቃታቸውን የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የፅህፈት ቤቱ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ኩልሱማ ቡርሃባ አሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት በማዕከላዊና ታችኛው አዋሽ በስጋት ቀጠናነት ከተለዩት 17 ወረዳዎች መካከል 10ሩ በጎርፍ አደጋ ተጠቅተዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም 19 ሺህ 656 ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው ከተፈናቀሉት በተጨማሪም በእንስሳት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ ባለፈም በጎርፉ ሳቢያ 51 ሺህ 659 ሰዎች ስጋት ውስጥ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ ከጎርፍ አደጋው ጋር በተያያዘ በ5 ወረዳዎች ምላሽ ተሰጥቷል ያሉት ምክትል ሃላፊዋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ የማድረግና ከመከላከያ ጋር በመተባበር በሄሊኮፕተር የነብስ አድን ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በዋናነትም በክልሉ ምላሽ ሰጭ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ከፌደራል መንግስት እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምግብ እና ምግብ ነክ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑም ገልጸዋል፡፡

እየወጡ ያሉ የአየር ትንበያ መረጃዎች በቀጣይ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አመላካች መሆናቸውን ተከትሎም ነዋሪዎችን ወደ ከፍተኛ ቦታዎች የማዘዋወር እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

ባለፈው አመት በአዋሽ ወንዝ ላይ አቅጣጫ የማስቀየር ስራ ቢሰራም በአካባቢው ከፍተኛ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ የጎርፍ አደጋው መከሰቱንም አውስተዋል፡፡፡

በመለሰ ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.