Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደሌለው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰብዓዊ መብት እና በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ በሉዓላዊ ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደሌለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡
 
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ቡድን በአልጄሪያ ኦራን ከተማ 8ኛ የአፍሪካ የሰላም እና ፀጥታ ከፍተኛ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል፡፡
 
ጉባኤው በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት እና በተ.መ.ድ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ተለዋጭ አባል አገራት መካከል በተ.መ.ድ የፀጥታ ምክር ቤት የአፍሪካን የጋራ ጥቅም ሊያስጠብቅ በሚችል ግንኙነት እና ትብብር ላይ አተኩሮ ተወያይቷል፡፡
 
8ኛው የአፍሪካ የሰላም እና ፀጥታ ከፍተኛ ጉባኤ ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት በምትመራው መድረክ ላይ አቶ ደመቀ ባቀረቡት ንግግር፤ በአሁን ወቅት በተ.መ.ድ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን ወደ ጎን እየተገፋ እንዲሁም አንዳንድ ሃያላን ሃገራት በራሳቸው ባለአንድ ወገን መርህ ላይ ተመስርተው በአፍሪካ ላይ የሚያደርጉት ያልተገባ ተጽዕኖ ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
 
“በሰብዓዊ መብት እና በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ በማድረግ በሉዓላዊ ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት መወገዝ ይኖርበታል፡፡” ብለዋል፡፡
 
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሃገራት በተ.መ.ድ የፀጥታ ምክር ቤት የተጫወቱት ሚና ገንቢ ቢሆንም፤ በሃያላን ሃገራት የሚርስባቸውን ጫና ተቋቁመው የአፍሪካ ሃገራትን ፍትሃዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲችሉ በተባበረ ድምጽ እና በተቀናጀ ተግባር ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
 
የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት መርህን መጋፋት ተቀባይነት እንደሌለው ጉባኤው በስፋት የመከረ ሲሆን፤ አሸባሪነትን በመደገፍ፣ ሙስና እና ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ መንግስት ለመቀየር የሚደረግ ህገወጥ እንቅስቃሴ አፍሪካውያን በቅንጅት መመከት እንደሚገባቸው ጉባኤው አስምሮበታል፡፡
 
ጉባኤው በኢትዮጵያና አንዳንድ ሃገራት ላይ የሚደረጉ ተመሳሳይ ጫናዎችን በማሳያነት የተመለከተ ሲሆን፥ አፍሪካውያን በፓን አፍሪካኒዝም መርህና አስተሳሰብ እየተመሩ ችግሩን በጋራ ሊመክቱ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።፡
 
እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በወሰደችው የህግ ማስከበር እርምጃን ተከትሎ ተጽዕኖ ለመፍጠር እና ማዕቀብ ለመጣል የሚደረጉ ጫናዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም።
 
“ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ የመፍታት አቅም እና ብቃት አላት።” ብለዋል አቶ ደመቀ።
 
አሸባሪ እና ወራሪው ሃይል ከውስጥ እና ከውጭ ካሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት የሚያካሂዱትን ዘመቻ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በአስተማማኝ ሁኔታ እየቀለበሱት መሆኑን በመጠቆም፤ ችግሩን በዘላቂነት የመፍታት ርብርቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል፡፡
 
ይሁንና አንዳንድ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና ተቋማት የሃሰት እና የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የሚያደርጉት ያልተገባ እንቅስቃሴ፤ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር ፈፅሞ የሚጋጭ እና የሚቃረን መሆኑን ጠቁመዋል።
 
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት በፈረንጆች አቆጣጠር በዴሴምበር ወር 2021 ዓ.ም በሊቀመንበርነት የምትመራ ሲሆን፤ ለወሩ የተያዙ አጀንዳዎችን የአፍሪካን ጥቅም ባስከበረ መልኩ እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቃለች፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.