Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ቀንድ እየተጠናከረ የመጣው የወደብ እና የጦር ሰፈር ግንባታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ቀንድ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ የመጣው የበርካታ ሀገራት የወደብ እና የጦር ሰፈር ግንባታ ቅርምት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ ከወዲሁ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በአውሮፓ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ላይ የማማከር ስራ የሚሰሩት ልዑል ዶክተር አስፋውወሰን አስራተ ካሳ እና በጀርመን ሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ እና አፍሪካ ባህል ጥናት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ዶክተር ጌቴ ገላዬ ኢትዮጵያውያን በዙሪያቸው አደጋ ባንዣበበት ፈታኝ ወቅት ከልዩነት ይልቅ አንድነታቸውን አስቀድሞ የመንቀሳቀስ ታሪካዊ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል ።
ቅድሚያ ወደ እራስ መመልከት ይገባል ያሉት ዶክተር ጌቴ ገለዬ ÷ ኢትዮጵያውያን በቂ ትኩረት ያልሰጡትን እምቅ ባህል እና ትውፊት ሌሎች ሀገራት እየተጠቀሙበት መሆኑን ልብ ማለት ይገባልም ነው የሚሉት፡፡
ለዚህ ደግሞ አማርኛ እና የግዕዝ ቋንቋዎች በጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጡ በማንሳት፥ ይህም የኢትዮጵያን ሃገር በቀል እውቀት ለመረዳት እና ለመጠቀም በማሰብ የሚደረግ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ከአንድነት ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከጀርመን ወጣቶች መቅሰም ያለባቸው የሀገር ግንባታ ልምድ አለ ይላሉ።
የጀርመን ወጣቶች በአዶልፍ ሂትለር ፖለቲካዊ ስርአት እና በበርሊን ግንብ ምክንያት ለ40 አመታት ለሁለት ተከፍለው መቆየታቸውን ለዚህ እንደማስታወሻ ያጣቅሳሉ፡፡
ይሁን እንጅ ከበርሊን ግንብ መፍረስ በኋላ ልዩነታቸውን አጥብበውና አንድ ሆነው ሰላማዊና ለሁሉም የምትመች ጠንካራዋን ጀርመን መገንባታቸውን ያስረዳሉ፤ ይህ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትልቁ መማሪያ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
ኢትዮጵያውያንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከግል እና ከቡድን ፍላጐት ስሜት በመውጣት ለብሔራዊ ጥቅም በአንድነት የሚቆሙበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ጌቴ የአፍሪካ ቀንድ የሃይል አሰላለፍ ሽኩቻን በማንሳት አሁን ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠት ያለበት ቀጠናዊ ጉዳይ አለ ሲሉም ያነሳሉ፡፡
አሁን ላይ በቀጠናው በርካታ የባህረ ሰላጤው እና የአውሮፓ ሃገራት የወደብና የጦር ሰፈር እየገነቡ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ጌቴ፥ ኢትዮጵያም በተለይም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው እና ሃገራዊ ደህንነቱ የቀጠናውን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ባይ ናቸው፡፡
በአውሮፓ በአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ዙሪያ በማማከር ስራ ላይ የሚገኙት ልዑል ዶክተር አስፋውወሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ዛሬ ላይ የደረሰቸው አባቶች ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ብሔራዊ ጥቅማቸውን በማስቀደማቸው ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻርም አንድነትን ማጠናከርና በተለይም አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት ስርአትን በመሰረታዊነት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አሁን ላይ ያለው አብዛኛው ወጣት የተዛባ ትርክት ሰለባ መሆኑን በመጥቀስም ከስርአት ትምህርት ጀምሮ ማሻሻያ በማድረግ የተዛባውን ትርክትም ማረምና ማስተካካል አስፈላጊ ስለመሆኑም አስምረውበታል፡፡
ይህ ትውልድ ከዚህ ደማቅ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ታሪክ ሊማር ይገባል ያሉት ልዑል ዶክተር አስፋውወሰን፥ የባህል፣ የዘርና የሃይማኖት ብዝሐነት ፀጋ እንጂ እርግማን አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
የአሁኑ ትውልድም ከተደቀኑበት ስጋቶች ነፃ ለመሆን መስራት አለበት በሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
በስላባት ማናዬ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.