Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ አልፏል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ አህጉር በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ መብለጡ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሚሊየን 348 ሺህ መብለጡን የሚያሳየው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ፤ ከእነዚህም ውስጥ 10 ሺህ 68ቱ በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ74 ሺህ ሲበልጥ፤ በአፍሪካም በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ480 ተሻግሯል።

በአፍርካ ከ990 በላይ ሰዎች ደግሞ ከወረርሽኙ ማገገማቸውንም ነው የዩኒቨርሲቲው መረጃ የሚያመላክት ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከ284 ሺህ በላይ ሰዎች አገግመዋል።

ከአፍሪካ አህጉር 1 ሺህ 686 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የያዘችው ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን፤ በሀገሪቱ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ውስጥ የ12 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 95 ሰዎች ማገገማቸውም ነው የተገለፀው።

በአልጄሪያም 1 ሺህ 423 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፥ 173 ሰዎች ህይወታቸው አልፎ፤ 90 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

በግብፅም እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 1 ሺህ 322 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም 259 ሲያገግሙ፤ 85 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

በሞሮኮም 1 ሺህ 120 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 81 ሰዎች ሲያገግሞ 80 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ወደ ምስራቅ አፍሪካ ስንመጣ ኬንያ 158 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ያስታወቀች ሲሆን፥ ከእነዚህም 4 ሰዎች ሲያገድሙ፤ 6 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

በጂቡቲ 90 ሰዎች፣ በኤርትራ 31 ሰዎች፣ በሶማሊያ 7 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን እስካሁን የተመዘገበ ሞት የለም።

በኢትዮጵያም እስከ ትናንትናው እለት ባለው መረጃ በአጠቃላይ ቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 44 የደረሰ ሲሆን፥ ከእነዚህም 4 ሲያገግሙ፤ 2 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.