Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ደረሰ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸውን ነው የገለጸው፡፡

በቫይረሱ ከተያዙ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ 36 ሺህዎቹ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በአህጉሪቱ በደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡

በዚህም በደቡብ አፍሪካ 679 ሺህ 716 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በሀገሪቱ ከ100 ሺህ ሰዎች 1 ሺህ 198 ያህሉ በቫይረሱ እንደሚያዙ ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም 590 ሺህ 71 ሰዎች ወይም 90 በመቶ የሚሆኑት ከቫይረሱ አገግመዋል ነው ያለው፡፡

በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ 16 ሺህ 938 ወይም 2 ነጥብ 49 በመቶዎቹ ህይወታቸውን እንዳጡ ድርጅቱ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡

ሞሮኮ 131 ሺህ 228፣ ግብጽ 103 ሺህ 575፣ ኢትዮጵያ 76 ሺህ 98 እና ናይጄሪያ 59 ሺህ 287 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘውባቸዋል፡፡

በአህጉሪቱ የመመርመር አቅም አነስተኛ በመሆኑ ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ለማወቅ አዳጋች መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡

እንደ ናይጀሪያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የሚገኝባቸው ሃገራትም የመመርመር አቅማቸውን ለማዳበር ሰሞኑን የኮሮና ቫይረስ ውጤትን ከ40 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ የሚያሳውቅ የመመርመሪያ ኪት ለመጀመር የተቆጣጣሪ አካሉን ፍቃድ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.