Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የመጀመሪያው የድሮን ፎረም በሩዋንዳ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የመጀመሪያው ሰው አልባ አነስተኛ በራሪ አካላት (ድሮን) ፎረም በሩዋንዳ እየተካሄደ ይገኛል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ፎረም ዘርፉን የተመለከተ ሲምፖዚየም፣ አውደ ርዕይ እንዲሁም በኪፉ ሃይቅ ዳርቻ የበረራ ውድድር ይካሄድበታል ተብሏል።

የሩዋንዳፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የድሮን ኢንዱስትሪ በአህጉሪቷ የሚታየውን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግር በዘመናዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንቱ ፎረሙ ችግሮችን ወደ በጎ እድል ቀይሮ ለመጠቀም በማሰብ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

ይህ እድል አፍሪካውያን በቴክኖሎጂ ታግዘው ሰፊ ስራ እንዲሰሩ ከማነሳሳቱም በተጨማሪ ህልማቸውን እንዲያሳኩ በር ይከፍታልም ብለዋል።

በፈረንጆቹ 2016 ሩዋንዳ ዚፕ ላይን ከተባለ ተቋም ጋር ድሮኖችን በመጠቀም ለድንገተኛ ጊዜ የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶችን እና የደም አገልግሎት ለመስጠት ስምምነት አድርጋ ነበር።

ድሮኖቹ ከህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በተጨማሪም ወባን ለመካላከል መድሃኒት በመርጨትና የግብርና ስራዎች ላይ በመሳተፍ የሩዋንዳ ገበሬዎችን እንደሚያግዙ ኦል አፍሪካን ድረ ገጽ አስነብቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.