Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የመንገደኞች የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎትን እንደገና ለማስጀመር ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የመንገደኞች የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎትን እንደገና ለማስጀመር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ እና የሱዳን የትራንስፖርተሮች ማህበር አመራር አባላት÷ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የመንገደኞች የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
አመራር አባላቱ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስጀመር ከሱዳን የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የመንገድ ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚህም በሱዳን በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸው÷ ሚሲዮኑ በኢትዮጵያ በኩል የሚመለከታቸው ተቋማት ተመሳሳይ ዝግጅት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት እና በዝቅተኛ ገቢ ለሚኖሩ ዜጎች የተሻለ የትራንስፖርት አማራጭ ለማቅረብ የመንገድ ትራንስፖርት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በመመካከር የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎቱን እንደገና ለማስጀመር ኤምባሲው እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.