Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ውይይት በጥሩ ውጤት መጠናቀቁ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና የልዑካን ቡድኖቻቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ  ከአውሮፓውያኑ ጥር 13 እስከ 15 ቀን 2020 በዋሽንግተን ዲሲ ሲያካሂዱት የነበረው ውይይት በጥሩ ውጤት መጠናቀቁን ነው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የገለፀው።

ውይይቱ የተካሄደው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቬን ሙንሺን እና የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት ነበር።

ውይይቱ ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረውን የቴክኒክ ውይይት በማስቀጠል በሶስቱ አገራት ዋና ከተሞች በአራት ዙር በውሃ ሃብት ሚኒስትሮች ሰብሳቢነት እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ በሶስት ዙር በተካሄዱት ውይይቶች ዙሪያ ሪፖርት ቀርቦ የስትራቴጂካዊ ውይይት በማድረግ በመግባባት ተጠናቋል።

ከዚህም በመነሳት በእስካሁኖቹ የድርድር ሂደቶች የነበሩትን ልዩነቶች በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ በመፍታት ወደ መጨረሻ ስምምነት ለመድረስ በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓል።

በቀጣይም በአውሮፓውያኑ ጥር 28 እና 29 በዋሽንግተን ዲሲ በመገናኘት የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፥ በመካከል ባለው ጊዜ ወቅት የሶስቱም አገራት የህግ ባለሙያዎች የተወከሉበት ቡድን በህግ ማዕቀፎቹ ላይ የጋራ ምክክር የሚያካሂድ ይሆናል።

በመጨረሻም በሶስቱም አገራት መካካል የበለጠ መግባባት፣ መተባበር እና መተማመን እንዲዳብር በጋራ ለመስራት በመግባባት ስሜት ውይይቱ ተጠናቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.