Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ የዲፕሎማሲ ጫናዎች መሻሻል አሳይተዋል-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ የዲፕሎማሲ ጫናዎች መሻሻል ማሳየታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የቻይና አፍሪካ የጋራ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ መሳተፏ እንደስኬት የሚቆጠር ነውም ብለዋል።

በሴኔጋሉ ጉባኤ ኢትዮጵያ እውነቱን ለተቀረው አለም ለማሳየት እድል ከፍቶላታልም ብለዋል።

እንዲሁም በዚህ ሰዓት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውም ኢትዮጵያ አሁንም ወዳጆች እንዳላት የሚያሳይና ሰፊ ትርጉም ያለው እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የ”በቃ” ዘመቻ አፍሪካዊ መልክ እንደያዘና በርካታ ተከታዮችን ከመላው ዓለም ማፍራቱንም አንስተዋል።

ከድል ማግስት የሚከበሩ የገናና የጥምቀት በዓላትን ለማክበርም 1 ሚሊየን ዲያስፖራዎች መጠራታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው በመምጣት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያደረጉት ሀብት የማሰባሰብ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው ያመለከቱት።

አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራችን በቅርቡ በሚከበሩ በዓላት ላይ እንዲገኙ ጥሪ መደረጉንም አስታውሰዋል።

በአገራችን የተገነቡ ልዩ ልዩ የቱሪስት ምስህብ ያላቸውን ፓርኮችና ትናንት ከወራሪው ቡድን ነፃ የወጣችውን ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን እንዲጎበኙም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበው፥ ሲመለሱም የሀገሪቱን ሰላማዊነት ለቀሪው ዓለም እንዲመሰክሩም ነው የጠየቁት።

በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ከየትኛውም የዓለም ከተሞች በተሻለ ደረጃ ሰላም የሰፈነባት መሆኗንም ነው ያስታወቁት።

በአፈወርቅ እያዩና ዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.