Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ተመዘገበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝ ከተከሰተ ጀምሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር መመዝገቡን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
የጤና ሚኒስትሯ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና በወረርሺኙ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እያሻቀበ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ የዴልታ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱና ኅብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ መላላት ለወረርሺኙ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችለውን ክትባት አለመውሰድና ከቫይረሱ ጋር የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችም ለቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ እየተጠጋ መሆኑን ጠቁመው ባለፈው ሳምንት ብቻ 308 ሰዎች በወረርሺኙ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል።
ይህም በየቀኑ በአማካይ 44 ሰዎች በወረርሺኙ ሳቢያ ህይወታቸውን እያጡ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።
ወረርሺኙ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛ የሞት ምጣኔ መሆኑንም ነው ዶክተር ሊያ ያስረዱት።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው በተለይም ደግሞ ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ለወረርሺኙ የመጋላጥና የመሞት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ከተከተቡ ሰዎች ይልቅ በወረርሺኙ ለመያዝ 4 ነጥብ 5 እጥፍ፣ በወረርሺኙ ተይዘው ሆስፒታል የመተኛት 10 እጥፍ እንዲሁም በወረርሺኙ የመሞት 11 እጥፍ አጋጣሚ ሊኖራቸው እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ሚኒስትር አብራርተዋል።
ከሰኔ ወር አጋማሽ እስከ ነሓሴ አጋማሽ 2013 ዓ.ም ጤና ሚኒስቴር ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በወረርሺኙ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያልተከተቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ሕዝቡ ክትባት እንዲከተብና መንግሥት ወረርሺኙን ለመከላከል ያወጣቸውን መመሪዎያዎች በመተግበርና የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንዳለበት ነው የገለጹት።
መጪው ጊዜ ትምህርት የሚከፈትበት መሆኑን አንስተው በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድ ወረርሺኙን መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በዓሉን ወረርሺን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲያከብሩ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.