Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ 3 ሰዎች ተገኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 25 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይህ መረጃ እስከ ተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ በአጠቃላይ 1013 የላቦራቶሪ ምርመራ ያደረገ ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 66 የላብራቶሪ ምርመራ አካሄዶ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት (3) ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡

በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25 መድረሱን ነው የገለፀው።

በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሁለት ግለሰቦች የ30 ዓመትና የ36 ዓመት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ በተመሳሳይ በረራ ከዱባይ በመጋቢት 15 ፣2012 ዓ.ም ወደ ሀገር የገቡ ሲሆን በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን የበሽታውን ምልክት ታይቶባቸው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ሶስተኛዋ ታማሚ የ60 ዓመት እድሜ ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ መጋቢት 6፣2012 ዓ.ም ከፈረንሳይ የተመለሱና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

ሶስቱም ታማሚዎች በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛሉም ብሏል።

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ሃያ አንድ (21) ታማሚዎች ሲኖሩ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለት ታማሚዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን ሁለት ታማሚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመዋል። ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉም ብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.