Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ በሙሉ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ በሙሉ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፥ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ መያዙ የተረጋገጠም ሆነ በለይቶ ማቆያ ማዕከሉ ሆኖ ክትትል የሚደረግለት ሰው የለም ብሏል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ በተቋሙ ማድረግ የጀመረ በመሆኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊላክ የነበረ የ3 ሰዎች ናሙና ምርመራ በማድረግ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉንም ገልጿል።

በተጨማሪም የሶስቱ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልከው የነበሩ ናሙናዎች ውጤት እንደደረሰው የገለፀው ኢንስቲትዩቱ፥ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል።

የኮሮና ቫይረስን በሽታ የመከላከል ዝግጁነትን ለማጠናከርም ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በአዲስ አበባ ለሚገኙ 13 ሆስፒታሎች የተለያዩ ግብዓቶችን ማሰራጨቱን በመግለፅ፤ ለክልል ሆስፒታሎችም ለማሰራጨት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ እስከ አሁን ድረስ 31 ጥቆማዎች ለኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰው ማጣራት ተደርጎባቸዋል ያለው ኢንስቲትዩቱ፥ ከነዚህ ውስጥ 14ቱ በልየታ ቆይተው ናሙናቸው ተመርምሮ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ከለይቶ ማቆያ ማዕከሉ እንዲወጡ ተደርጓል ብሏል።

የበሽታውን ልየታ ስራ ለማጠናከር የልየታ ቡድኑን ለሚቀላቀሉ የጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና  መሰጠቱንም ነው ያስታወቀው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ብሔራዊ ግብረ ሃይል ጥር 29 2012 በኮሮና ቫይረስ ቅድመ መከላከል ዙሪያ ውይይት ማድረጉንም ነው ኢንስቲትዩቱ ያስታወቀው።

ለሆቴሎች፣ ታክሲ ሾፌሮች እና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።

ሕብረተሰቡ በሀገራችን እስካአሁን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለመኖሩን አውቆ ሳይዘናጋ የበለጠ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የኮሮና ቫይረስ ከታየባቸው ሀገራት የመጡ መንገደኞች ወይም በዚህ ቫይረስ ከተያዙ ግለሰቦች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ላይ የበሽታው ምልክቶች (ትኩሳት፣ ሳል፤ የትንፋሽ መቆራረጥ፣ የመተንፈስ ችግር) ከታዩ፣ ማንኛውም የሕብረተሰቡ አካል በአስቸኳይ በ8335 ነጻ የስልክ መስመር ላይ በመደወል ሪፖርት እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።

በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት፣ እስከ የካቲት 01/2012፣ ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 37 ሺህ 494 ሲሆንእስከ ዛሬ  ድረስ 813 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.