Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 ደረሰ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 መድረሱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ኮቪድ19ን በተመለከተ በዛሬ እለት መግለጫ ሰጥቷል

መጋቢት 3/2012 ዓ.ም የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው በሀገራችን ከተገኘ ወዲህ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ አራት (4) ተጨማሪ ሰዎች በመገኘታቸው በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስራ ስድስት (16) ደርሷል፡፡ የታማሚዎች ዝርዝር ሁኔታ፡-

ታማሚ 1፡ የ72 ዓመት ሞሪሸሳዊ ሲሆኑ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ከኮንጎ ብራዛቪል የተመለሱ ናቸው፡፡ መጋቢት 13፣2012 ዓ.ም ወደ ጤና ተቋም የሄዱ ሲሆን ተቋሙም ለኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት በማደረጉ በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ ታማሚውም በለይቶ ማከሚያ ውስጥ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከታማሚው ጋር ግንኙነት የነበራቸው 6 ሰዎች በክትትል ላይ የሚገኙ ሲሆን ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌሎች ሰዎችን የማጣራት ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ታማሚ 2፡ የ61 ዓመት የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ከታማሚው በተገኘው መረጃ መሠረት ግለሰቡ የውጭ የጉዞ ታሪክ ባይኖራቸውም በስራ ባህሪያቸው ምክንያት ከአንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ጋር ግንኙነት ነበራቸዉ፡፡ ግለሰቡ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም የህመም ስሜት ሲሰማቸው ራሳቻውን አግልለው እንደቆዩና መጋቢት 16፣2012 ዓ.ም ወደ ጤና ተቋም የሄዱ ሲሆን ተቋሙም ሪፖርት ባደረገው መሰረት በላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ታማሚው በለይቶ ማከሚያ ውስጥ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከታማሚው ጋር ግንኙነት የነበራቸው 24 ሰዎች በክትትል ላይ የሚገኙ ሲሆን ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌሎች ሰዎችን የማጣራት ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ታማሚ 3፡ የ28 ዓመት ኢትዮጵያዊት ስትሆን የመጨረሻ ጉዞዋም መጋቢት 12፣ 2012 ዓ.ም እስራኤል ሀገር ደርሳ የተመለሰች ናት፡፡ ግለሰቧም በቀን 16፣ 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዙዋ ተረጋግጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ታማሚዋ በለይቶ ማከሚያ ውስጥ የህክምና ክትትል እየተደረገላት ይገኛል፡፡ ከታማሚዋ ጋር ግንኙነት የነበራቸው 7 ሰዎች በክትትል ላይ የሚገኙ ሲሆን ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌሎች ሰዎችን ማጣራት ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ታማሚ 4፡ የ24 ዓመት ኢትዮጵያዊት ስትሆን የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላት ቢሆንም የበሽታው ምልክት ከታየባቸው ሰዎች ጋር የነበራት ግንኙነት እየተጣራ መሆኑ እና ግለሰቧም በቀን 17፣ 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዙዋ ተረጋግጧል፡ በአሁኑ ወቅት ታማሚዋ በለይቶ ማከሚያ ውስጥ የህክምና ክትትል እየተደረገላት ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት እስከ አሁን 718 የላራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን 33 በ24 ሰዓት ( መጋቢት 17 ጥዋት 1፡00 ሰዓት እስከ መጋቢት 18 ጥዋት 1፡00 ሰዓት) ውስጥ የተከናወነ ነው፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ማግኘት ይቻላል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.