Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በ11 ወራት የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶችን በማክሸፍ የ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በ11 ወራት ከተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከ97 በመቶ የሚልቀውን በማክሸፍ የ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ገለጸ።

የሳይበር ጥቃቱ በፋይናንስ እና የሚዲያ ተቋማት ላይ በብዛት ዒላማ ያደረገ መሆኑም ታውቋል።

የሳይበር ምሕዳር በባህሪው ድንበር የለሽና ኢ-ተገማች በመሆኑ ዓለም በዚህ መጠነ-ሰፊና ተለዋዋጭ ወንጀል በየቀኑ በአማካይ 16 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ሀብት ታጣለች።

የሳይበር ወንጀል በ2015 በዓለም ላይ 3 ትሪሊየን ዶላር ካደረሰው ኪሳራ በእጅጉ እያንሰራራ መጥቶ በ2021 ደግሞ 6 ትሪሊየን ዶላር አሳጥቷል።

በየዓመቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው ዓለም አቀፍ የሳይበር ወንጀል በ2025 ከ10 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር በላይ ሊያሳጣ እንደሚችል ተገምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰሞኑን በሰጡት ማብራሪያ ፥ በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5 ሺህ 860 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ በየቀኑ በቢሊየን ዶላር የሚያሳጣው የሳይበር ጥቃት ለኢትዮጵያም ፈተና መሆኑን ማስረዳታቸው ይታወሳል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ፥ የሳይበር ወንጀል በኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ።

በዚህም በ2011 ዓ.ም 790፣ በ2012 ዓ.ም 1 ሺህ 80፣ 2013 ዓ.ም 2 ሺህ 900 የሳይበር ጥቃቶች መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት 11 ወራት ደግሞ 6 ሺህ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከየት እንደተሞከሩና የወንጀሉን ባለቤቶች በቀላሉ ለመለየት ባይቻልም ያነጣጠሩባቸው ተቋማት መለየታቸውንም ጠቁመዋል።

በሳይበር ጥቃቱ በተለይም በባንክና የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ማነጣጠሩን ጠቅሰው ፥ የሚዲያ ተቋማትም ዒላማ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

የመንግሥት ቁልፍ መሰረተ-ልማቶች፣ የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ የፌደራልና የክልል የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ተቋማትም በርከት ያለ ጥቃት ተሞክሮባቸዋል ተብሏል።

ከተሞከሩ 6 ሺህ የሳይበር ጥቃቶች መካከል ከ97 በመቶ በላይ ሙከራዎችን በማክሸፍ የ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ሊደርስ የነበረውን አደጋ የማዳን አቅም እየጎለበተ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፥ የሳይበር ወንጀል ሁልጊዜም ኢ-ተገማች በመሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤቱ በሰጠቱት ማብራሪያ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከመደበኛ የሰራዊት ግንባታ ጎን ለጎን የሳይበር ጥቃትን የሚከላከል አቅም መገንባት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.