Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ከማንነትና ከራስ አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚካሄደው ጥናት በመላ ሀገሪቷ 68 አካባቢዎችንን እንደሚሸፍን ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቷ ከማንነትና ከራስ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከመሰረቱ መፍታት የሚያስችል ሀገራዊ የጥናት ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ጀምሮ ለማጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እንደሚሰሩ ተገለጸ።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ 24 ዩኒቨርሲቲዎች የአስተዳደር ወሰን፣ ማንነትና ራስን በራስ በማስተዳደር ላይ የሚካሄደውን ሀገራዊ የጥናት ፕሮጀክት በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ እንዳሉት፤ ጥናቱን በፍጥነት ለማካሄድ በጋራ መስራቱ የተሻለ ነው።
“ስምምነቱ ያስፈለገው የአስተዳደር ወሰን፣ ማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮችን በጥናትና ምርምር መፍታት በማስፈለጉ ነው” ብለዋል።
ጥናቱ የሚካሄደው የህዝቦችን እኩልነትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመፍጠር በሚወሰዱ መፍትሔዎች ላይ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብም እንዲቻል ነው።
በቀጣይ አስተዳደራዊ ወሰን የሚወሰንበትንና የሚለወጥበትን ግልጽ አሰራር ለመፍጠር በጥናት ማረጋገጥ ማስፈለጉም ሌላው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአስተዳደራዊ ወሰኖች ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች የሚፈቱበትን መንገድ ማመላከትና በህዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ምርምር ለማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል።
ዶክተር ጣሰው ”በቀጣይ አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭት መነሻ እንዳይሆኑ ምክረ ሃሳቦች ይሰነዝራሉ” ብለዋል።
ጥናቱ በሁሉም ብሔር ብሄረሰብ፣ በዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም በድንበር አካባቢዎች እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የሚካሄደው ጥናት በሀገሪቷ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ዘላቂና የማያዳግም መፍትሔ ለማምጣት የሚከናወን መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በጥናቱ 68 ቦታዎች በመላ ሀገሪቷ የሚካለሉ ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻም ጥናቱ እንደሚጠናቀቅ ኢዜአ ዘግቧል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ከፊርማ ስነ ስርዓቱ በኋላ እንደተናገሩት የጥናቱ ዓላማ በዋናነት ይህንና መሰል ችግሮችን ማስወገድ መሆኑን ተናግረዋል።
“በዚህም በየአካባቢው በአሁኑ ወቅት በማንነትና ከራስ አስተዳደር ጋር እያጋጠሙ ያሉ ተያያዥ ችግሮችን መቅረፍና ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ብልጽግና ማምጣት ነው” ብለዋል።
ጥናቱን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመለመሉ ተመራማሪዎች የሚያካሂዱት ሲሆን የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ጥናቱን በቅርበት እንደሚከታተሉት ተጠቁሟል።
ጥናቱን ለማከናወን 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተመደበ ሲሆን ገንዘቡም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ወጪ እንደሚደረግ ተመልክቷል።
ከዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ጋር በገባው ውል መሰረት ጥናቱን የሚመራው ይሆናልም ነው የተባለው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.