Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የሂሳብ ሙያ ልማትን ይደግፋል የተባለ የ450 ሺህ ፓውንድ ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ የሂሳብ ሙያ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲተገበር የ450 ሺህ ፓውንድ የሂሳብ ሙያ ልማት ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለጸ።

የተመሰከረላቸው የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ማሕበር ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ  በጋራ ፕሮጀክቱን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂክመት አብደላ ÷ ፕሮጀክቱ የዘርፉን አጠቃላይ ሁኔታ መለወጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሂሳብ አያያዝ አተገባበር አለመኖሩ ብዙ ችግሮች ሲያስከትል ነበር ነው ያሉት።

ለገንዘብ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከተቋቋመ በኋላ  ይህን ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ደረጃውን የጠበቀ ክህሎት እንዲገነቡና ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያላቸውን የልማት ተቋማት ውጤታማ ለማድረግ የሚረዳ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ፕሮጀክቱ በቀጣይ ኢትዮጵያ ለመተግበር ያቀደችውን የካፒታል ገበያና የልማት ተቋማትን ወደ ግል የማዛወር እንቅስቃሴ ለማገዝ የሚረዳ እንደሆነም ነው የገልጹት።

ጠንካራ የኦዲትና የሂሳብ አያያዝ ስርዓት በአገሪቷ ሲኖር የፋይናንስ ስርዓቱ በትክክለኛ የፋይናንስ መግለጫ ስለሚደገፍ ባለሃብቶች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች አስተማማኝ እንዲሆን እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የተመሰከረላቸው የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ማሕበር የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዮዲት ካሳ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ይላሉ።

አንደኛው በቀጣይ ወደ ስራ ለሚገባውና በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ስር ለሚተዳደረው የ’ሂሳብ አያያዝና ኦዲት’ ኢኒስቲትዩት የሚደራጅበትን ስልት ማዘጋጀት ነው ብለዋል።

ይህም በአንድ ዓመት ውስጥ የሚከናወን ሲሆን ስልቱም የዓለም ዓቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ በማደረገ መልኩ ይቀረጻል ብለዋል።

ሁለተኛው በፕሮጀክቱ አማካኝነት የሚከናወነው ተግባር የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሚቆጣጠራቸውን ድርጅቶች ደረጃውን የጠበቀ መቆጣጣሪያ ስልት መቅረጽ መሆኑንም ወይዘሮ ዮዲት አብራተዋል።

 

ይህ ሲሆን የካፒታል ገቢያ ሂደቱን፣ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ ያለውን ተሳትፎ እንዲሁም ጥቅል ስርዓት ለማበጀት ይረዳል ሲሉም አስረድተዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው 500 ሂሳብ አያያዝ አዋቂዎችና ከ150 የማይበልጡ ኦዲተሮች እንደሚገኙም ተመላክቷል።

የተመሰከረላቸው የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ማሕበር በአፍሪካ በሩዋንዳ ተመሳሳይ ስራ የሰራ ሲሆን በኤሺያ ደግሞ በአፍጋኒስታን መሰል ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.