Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2018 80 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል- ሪፓርት

አዲስ አበባ ፣ ጥር 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ግምገማ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የመንገድ ደህንነት ልዩ ልዑክ አስተባባሪነት ተካሂዷል።

በግምገማው የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ብቃት ግምገማን የተመለከተው ሪፓርት የቀረበ ሲሆን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ፣ የተመድ ዋና ፀሃፊ የመንገድ ደህንነት ልዩ ልዑክ ጄይን ቶደት እና ሌሎችም በበይነ መረብ ተሳታፊ ሆነዋል።

ጄይን ቶደት የመንገድ ደህንነት ብቃት ግምገማ ሀገራት የመንገድ ደህንነት አስተዳደር አቅማቸውን እና ብሄራዊ የመዝገብ አያያዛቸውን እንዲያሻሽሉ ለማስቻል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለዚህ ፕሮጀክት ድጋፍ ከሚደረግላቸው አራት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስተዋል።

ወይዘሮ ዳግማዊት በበኩላቸው ሪፓርቱ የኢትዮጵያን የመንገድ ደህንነት ሁኔታ ለመገምገም እና በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎችን ለመለየት ያስችላል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከትራፊክ አደጋ በኋላ በሰዓቱ እና በውጤታማ አገልግሎቶች ማግኘት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዚህም የሶስተኛ ወገን የጤና መድህን ዋስትና፣ ቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት እና ሌሎች ስራዓቶችን  እየዘረጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የመንገድ የትራፊክ አደጋ እየጨመረ እንደሚገኝ ነው የሚያመለክተው።

በፈረንጆቹ 2010 በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ የ2 ሺህ 541 ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ሪፓርቱ ያመለከተ ሲሆን በ2018 የተመሳሳይ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 4 ሺህ 597 ደርሷል።

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2011 እስከ 2020 የሚቆይ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ እና የተግባር አቅድ አዘጋጅታ እንደነበረ ያመለከተው ሪፓርቱ እቅዱ ብዙም ስኬታማ እንዳልነበረ አመልክቷል።

ደህንነቱ ከተጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ በ2018 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያወጣው ሪፓርት 72 በመቶ የሚሆነው የመንገድ ትስስር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያመለክታል።

21 በመቶ የሚሆነው የመንገድ ትስስር ደግሞ መልካም በሚባል ደረጃ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ቀሪው 7 በመቶ መንገድ ችግር ያለበት መንገድ መሆኑን ሪፓርቱ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራምን በመቅረፅ በሀገሪቱ የመንገድ የመሰረተ ልማትን ለማሻሻል ባለፉት 20 ዓመታት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክቷል።

እንዲሁም በትራፊክ አደጋ የሚደርሰው የሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.