Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ቋንቋዎችን ለማበልጸግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ ስጋት የተደቀነባቸውን ቋንቋዎች በመለየት የመሰነድና እንዳይጠፉ የማበልጸግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ አስታወቀ።

አካዳሚው 50ኛ ዓመት የጥናትና ምርምር ጉዞውን የሚዘክር ክብረ-በዓል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ አክብሯል።

የአካዳሚው ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አድገህ÷ አካዳሚው በኢትዮጵያ ያሉ ቋንቋዎች እና ባህሎች እንዲበለጽጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለትውልድ እንዲተላለፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአገሪቱ ሰላሳ የሚደርሱ ቋንቋዎች ለመጥፋት አደጋ ስጋት የተጋለጡ መሆናቸው መለየቱን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ አንድ ቋንቋ ከትውልድ ወደ ትውልድ ካልተላለፈ፣ ዝቅተኛ ተናጋሪዎች ካሉት እና በሌሎች የቋንቋ ማበልጸጊያ ሂደቶች ጥቅም ላይ ካልዋለ የመጥፋት አደጋ ውስጥ መሆኑን ያሳያል።

በዚህም የሥርዓተ-ጽህፈት የሌላቸውን ቋንቋዎች እንደ ቋንቋ ባህሪያቸው በጥናት ላይ በመመስረት በግዕዝና በላቲን ፊደላት ሥርዓተ-ጽህፈት የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

አነስተኛ ተናጋሪ ላላቸው ቋንቋዎች ጭምር መዝገበ-ቃላት በማዘጋጀት ቋንቋዎቹ ከአፍ መፍቻነት ባለፈ ለትምህርት መስጫነት እንዲውሉ አካዳሚው የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቋንቋዎቹ እንዳይጠፉ በጽሑፍ የመሰነድ እና በሌሎች የቋንቋ ማበልጸጊያ ስልቶች እንዲዳብሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የተናጋሪዎቹ ሕዝብ ባህል እንዲታወቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና÷ ባህሎቻችንና ቋንቋዎቻችንን በማልማት ለማኅበረሰብ አገልግሎት ያላቸውን ፋይዳ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.